የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ2011 በጀት ከ346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ወሰነ

75
አዲስ አበባ ግንቦት 25/2010 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 48ኛ መደበኛ ስብሰባው የ2011 በጀት ዓመት ከ346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ወሰነ፡፡ በዚህ መሰረት በቀጣይ በጀት ዓመት በመንግሥት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች 346,915,451,948 (ሦስት መቶ አርባ ስድስት ቢሊዮን ዘጠኝ መቶ አስራ አምስት ሚሊዮን አራት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ አርባ ስምንት) ብር እንዲሆን ምክር ቤቱ ወስኗል። ከዚህ ውስጥም ፡-
  • ለመደበኛ ወጪዎች 91,675,160,588 ብር፣
  • ለካፒታል ወጪዎች 113,635,559,980 ብር፣
  • ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 135,604,731,380 ብር
  • እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 6 ቢሊዮን ብር  ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡
ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ጸድቆ ተግባራዊ እንዲሆን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል።
  • ባለፈው ዓመት ከጸደቀው በጀት ጋር ሲነፃጸር የ 3 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ምክር ቤቱ በተጨማሪም በምህረት አሰጣጥና አፈፃጸም ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ላይ መክሮ ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም የማኅበረሰቡን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የህዝቡን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ምህረት ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ መክሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቀው መርቶቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም