ህብረቱ ለኢትዮጵያ ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ሊያደርግ ነው

103

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2011 የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ተስማማ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ሚስተር ኤሪክ ሃበርስ ናቸው።

የድጋፍ ስምምነቱ 10 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 320 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ሲሆን በኢትዮጵያ እየተተገበረ ላለው የማህበራዊ ተጠያቂነት መርሃ-ግብር ይውላል ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እንዳሉት መርሃ-ግብሩ ህብረተሰቡ የራሱን መብት አውቆ በተለይም በመሰረታዊ አገልግሎት አገልጋዩን እንዲጠይቅ አቅም ለመፍጠር የሚሰራ ነው።

የዜጎችን አቅም መገንባትና ፈጻሚው አካል ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ አካል መሆኑን አብራርተዋል።

በመርሃ-ግብር አንድና ሁለት 233 ወረዳዎችን መድረስ የተቻለ ሲሆን በሶስተኛው መርሃ-ግብር 500 ወረዳ ተደራሽ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ተግባራዊ በተደረገባቸው ወረዳዎች አገልግሎት ፈላጊው አገልግሎት ሲጪውን የመጠየቅ ልምዱ በመሻሻሉ ሶስተኛውን መቀጠል እንዳስፈለገ አንስተዋል።

የአውሮፓ ህብረት በቀጣይም በኢትዮጵያ እየተደረገ ላለው ለውጥ 100 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጋፍ እንደሚያደርግ ማስታወቁን በመጠቆም ለዚህም መርሃ-ግብር እየተቀረጸ መሆኑንና ከመስከረም 2012 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ሚስተር ኤሪክ ሃበርስ በበኩላቸው ህብረቱ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለውጥ መደገፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በጤና፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በስራ እድል ፈጠራና በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደሚፈልግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት መርሃ-ግብር ሶስት በቀጣዮቹ አምስት አመታት ከባለድርሻ አካላትና ለጋሾች ጋር በመሆን እንደሚተገበር ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም