በዲጂታል ኢኮኖሚው ላይ ተጨባጭ ስራዎች መስራት የሚያስችል መሰረት ተጥሏል ተባለ

458

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2011 ባለፈው አንድ ዓመት በዲጂታል ኢኮኖሚው ላይ ተጨባጭ ስራዎች መስራት የሚያስችል መሰረት መጣሉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ‹‹ከመጋቢት እስከ መጋቢት›› በሚል ባለፈው አንድ አመት የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት እንደገለጹትም በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂው ዘርፍ 81 ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ ሀብት እያመነጨ ነው።

በዓለም ላይ እየመነጨ ካለው ሀብት አብዛኛው ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ላይ መሰረት ካደረጉ ዘርፎች እንደሆነና በተለይም አሁን ዲጂታል ኢኮኖሚው የዓለምን የኢኮኖሚ ዘርፎችን እየመራ ይገኛል ብለዋል።

ለአብነትም በዓለማችን ካሉ 10 ትልቅ ኩባንያዎች ስምንቱ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንደሆኑ አንስተው ዓለማችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ያለ ዲጂታል ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት ማሰብ እንደማይቻልም ጠቅሰዋል።

መንግስትም ይህን በመረዳት ለውጡን ተከትሎ ባለው አንድ ዓመት ዲጂታል ኢኮኖሚውን መልክ የማስያዝ ስራ ሲሰራ እንደነበር ተናግረዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ንግድ (ኢ-ኮሜርስ) ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት መከናወናቸውን በተለይም የዲጂታል የገንዘብ ክፍያ አገልግሎቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ወጣቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው የስራ እድል እንዴት ማግኘት እንደሚችሉና ሀብት መፍጠር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ወጣቶችም በግብርና፣ ጤና፣ትራንስፖርትና ግንባታ ዘርፎች የተለያዩ መተግበሪያዎችን፣ ሶፍትዌሮችንና ሲስተሞችን በመፍጠር ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙም ነው ያስረዱት።

በአጠቃላይ ዲጂታል ኢኮኖሚውን የሚያስተዳድር አዋጅ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን በተለያዩ ደረጃዎች በአዋጁ ዙሪያ ውይይት ሲደረግ ቆይቶ በቀጣዩ ሳምንትም በጋራ የመንግስትና የግል ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የውይይት መድረክ እንደሚዘጋጅም ጠቅሰዋል።

አዋጁ የዲጂታል ክፍያና ግብይት ስርዓት፣ የዲጂታል ታክስ፣ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የግለሰቦች መብት እንዳይጣስ መጠበቅና ሌሎች ጉዳዮችም ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀው አዋጁ በተያዘው ዓመት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።

እነዚህ ባለፉት አንድ ዓመታት የተከናወኑ ተግባራቶች በቀጣይ በዲጂታል ኢኮኖሚው ዘርፍ ለማሳደግ ለሚሰሩ ስራዎች መሰረት የጣለና በአንድ ዓመት ውስጥ ከተሰሩ ስራዎች እንደ ትልቅ ስኬት የሚታይ እንደሆነም አመልክተዋል።

ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ ቡና በኤሌክትሮኒክስ ንግድ (ኢ-ኮሜርስ) በዓለም ገበያ ላይ እንዲሸጥ በማድረግ የገበሬዎችን ኑሮ ለማሻሻልና ኢትዮጵያ አሁን ከቡና እያገኘች ያለውን የውጭ ምንዛሪ በአራት እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

በኢንፎርሜሽና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የቢሮ አሰራር ወረቀት አልባ እንዲሆንና ለዜጋው የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ እንደነበሩም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

ሚኒስትሩ በሁለትዮሽ ግንኙነቶችና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራት፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና ጥቅም ላይ በማዋል፤ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በመደገፍ እና ወደ ተግባር እንዲገቡ በማድረግ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

ግብርናውን ለማዘመን የተሰሩ ስራዎች በተለይም የአፈር ማዳበሪያ እና አሲዳማነትን ማከሚያ ቴክኖሎጂ ሙከራና ለ20 ትውልድ የሚሆን የማሽላ ዝርያ ምርምርም መካሄዱን አመልክተዋል።

ቴክኖሎጂን የሚጠቀም የተቀናጀ ግብርና፤ በእጅ የሚገፋ ማረሻ፤ ዘመናዊ ማጨጃ፤ የሴቶችን ጫና የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎች ማላመድ በአመቱ የተከናወኑ ስራዎች ናቸው ብለዋል።

በተለይም ቴክኖሎጂ ለሴቶች፤ ሴቶች ለቴክኖሎጂ በሚል ስራዎች የሴቶችን ጫና የሚያቃልሉ የቴክኖሎጂ ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቅሰዋል።

የኤሌክትሮኖክስ ግብይት፤ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ስርዓት ዝርጋታ፤ የኢኖቬሽን ማበልፀጊያ ማዕከላት ውስጥ እየበለፀጉ የሚገኙ ምርቶች፤ የኢኖቬሽን ማዕከል ግንባታ በትኩረት እየተሰራባቸው ያሉ መስኮች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በኢኖቬሽን ማዕከል ግንባታ፤ የሳተላይት ቴክኖሎጂ መሰረት የመጣል፣ ብሄራዊ የመረጃ ማዕከል ግንባታና የሳይንስ ካፌዎች ላይ የጀመሯቸውን ተግባራት ዳር የማድረስ ስራም ተሰርቷል ነው ያሉት።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራና የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በዚህም ረገድ ሚኒስትሩ በ2011 እና በ2012 ዓ.ም እስከ ሁለት ሺህ የቴክኖሎጂ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም ከ20 ሺህ በላይ የቴክኖሎጂና የስራ እድል ፈጠራና ሁለት ቢሊዮን ዶላር የቴክኖሎጂ ሀብት ለመፍጠር በማቀድ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

ይህንም ለማሳካት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚው ምህዳር መስፋት ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

ቴክኖሎጂን ያለመጠቀም ችግር ጊዜው የደረሰባቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ፈጠራዎችን ህዝቡ ካለው ወግ አጥባቂነት አንጻር ለመቀበል ያለው ፍላጎት ደካማ መሆን ባለፈው አንድ ዓመት የገጠመ ፈተና ነው ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዘርፉ እንዲያድግ ከአምስት ዓመት በፊት ከእርምጃ ወደ ሩጫ መርህ በሚል ሚኒስትሩ ኢኮኖሚውን ለማሳደግና ለመገንባት የሚያስችል ተግባር እያከናወነ እንደሆነም አክለዋል።