በምዕራብ እና በምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች የተከሰተውን የአሜሪካን መጤ ተምች የመከላከል ስራ እየተካሄደ ነው

2524

ሐረር/ጭሮ ግንቦት 25/2010 በምዕራብ እና በምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች ከ6ሺህ ሄክታር በሚበልጥ  የእርሻ መሬት ላይ የተከሰተውን የአሜሪካን መጤ ተምች የመከላከል ስራ እየተካሄደ  መሆኑን ተገለጸ፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሁለቱ ዞኖች ተምቹን  ለመከላከል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ወልደየስ እንደገለጹት በ5 ሺህ 220 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ ተምች ተከስቷል፡፡

በሁለት ሳምንታት ውስጥም  በዞኑ ስምንት ወረዳዎች የተስፋፋው ተምች በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ ለማስወገድ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በባህላዊ መንገድም ተምቹን ለመከላከል እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴም አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ መምህራንና ሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

ተምቹ ከታየበት ቀን ጀምሮ እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ በአንድ ሺህ 300 ሄክታር  የበቆሎ ማሳ ከተምቹ ጸድቷል።

በመጀመሪያው ዙር መስኖ ልማት የታየው ተምች ወደ መኸር አዝመራ እየተዛመተ በመሆኑ  የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ወንድወሰ አስታውቀዋል።

በዞኑ የመሰላ ወረዳ አርሶ አደር መሐመድ ኢብሮ በሰጡት አስተያየት በመስኖ ያለሙት  ግማሽ ሄክታር የቆሎ ማሳ በተምቹ መወረሩን ተናግረዋል።

በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ  በፀረ ተባይ ኬሚካል ለማጥፋት ርጭት መጀመራቸውን  ተናግረዋል።

ተምቹ በፍጥነት እየተስፋፋ በመሆኑ ማሳቸውን ለመታደግ ልዩ ትኩረት ሰጥተው  እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ሱሌይማን አሚን ናቸው።

በዘንድሮ በልግና የመኸር እርሻ 130 ሺህ ሄክታር መሬት በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በአገዳ ሰብል መሸፈኑም ታውቋል።

በሌላ በኩልም በምስራቅ ሐረርጌ 10 ወረዳዎች ውስጥ የተከሰተውን ተምች  ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የመከላከል ስራ እየካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጿል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የአዝዕርት ጥበቃ ባለሙያ አቶ እስራኤል ዋኬኔ እንደተናገሩት ተምቹ በዞኑ ወረዳዎቹ በሚገኙ 76 ቀበሌ  ውስጥ በተዘራ  900 ሄክታር የሰብል መሬት ላይ ተከስቷል።

የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በባህላዊ መንገድ  በተከናወነው ስራ 311 ሄክታር መሬት ከተምች ነጻ መደረጉን ጠቁመው የተምቹ ስርጭቱ ከፍተኛ በሆነበት 86 ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ  ኬሚካል የመርጨት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ  በአሁኑ ወቅትም  የልማት ሰራዊት ቡድንን በማደራጀት በባህላዊ መንገድ ተምቹ የተከሰተበትን መሬትና ስርጭቱን የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የሜታ ወረዳ ግብርና ባለሙያ አቶ ታከለ ገለታ በበኩላቸው  በ12 ቀበሌዎች በመስኖ በለማ መሬት ላየ መከሰቱንና ወደ መኸሩ ወቅት እየሄደ በመሆኑ አርሶ አደርን በማንቀሳቀስ በባህላዊ  መንገደ  የመከላከሉ ስራን እያከናወን እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የማይጠፋ ከሆነ ኬሚካል እንደሚጠቀሙ አመልክተዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት ሳይንሰ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሙላቱ ዋጋሪ በበኩላቸው ተምቹ በአካባቢው እንደታየ ጉዳት ሳያደርስ ለቅሞ በተባይ በማስበላትና በሌሎች ዘዴዎች  መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ስለዚህም ዘዴ በሁለቱ ዞኖች ለግብርና ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጡ ነው፡፡

በመከላከሉ ረገድ በተለይ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሩ ማሳቸውን እለት ተዕለት መከታተል እንዳለባቸው ጠቁመው ተባዩም ሲከሰት በባህላዊ መንገድ መከላከል እንደሚገባና ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡