ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በአገር አቋራጭ ውድድሩ ለተሳተፉ ልዑካን የእራት ግብዣ አደረጉ

98

አዲስ አበባ ሚየዝያ 1/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በ43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ለተሳተፈው ኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን በብሔራዊ ቤተመንግስት የእራት ግብዣ አደረጉ።

በዴንማርክ አርሁስ ከተማ መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያ በውድድሩ 5 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 11 ሜዳሊዎችን በመሰብሰብ ከዓለም አገሮች አንደኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።

በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ67 አገሮች የተወጣጡ 582 አትሌቶች ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በውድድሩ ተሳትፎ አንጸባራቂ ውጤት ላስመዘገበው የልዑካን ቡድን የእራት ግብዣ ማድረጋቸውንና ላስመዘገቡት ውጤት ምስጋና ማቅረባቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኮሚቴው አመራርና አብላጫ ውጤት ላስመሰገቡ አትሌቶች የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት አበርክተዋል።

ውድድሩ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትርና በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ በሁሉም ርቀቶች ላይ ተካፍላለች።

በውድድሩ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር በአትሌት ሚልኬሳ መንገሻ የወርቅ ሜዳሊያ፣ በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ የዱላ ቅብብልና ቀሪዎቹ የወርቅ ሜዳሊያዎች ደግሞ በአዋቂ ሴትና በሁለቱም ጾታ ወጣት ቡድን የተገኙ ናቸው።

ሶስቱ የብር ሜዳሊያዎች በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር በአትሌት ደራ ዲዳ፣ በወጣት ሴቶች በ6 ኪሎሜትር በአትሌት አለሚቱ ታሪኩና በወጣት ወንዶች ደግሞ በአትሌት ታደሰ ወርቁ የተገኙ ውጤቶች ናቸው።

በአዋቂ ሴቶች በአትሌት ለተሰንበት ግደይ፣ በወጣት ሴቶች ፅጌ ገብረሰላማና በአዋቂ ወንዶች የቡድን ውጤት ሶስቱን የነሐስ ሜዳሊያዎች ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም