የምርቶችን ጥራት ለማረጋገጥ እንዲቻል የ168 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ፀደቁ

232

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 1/2011 የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ብሄራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት የምርቶችን ጥራት ለመቆጣጠርና ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ 168 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን ማጽደቁን አስታወቀ።

ኤጀንሲው ደረጃዎቹን ያዘጋጀው ከሚመለከታቸው ከባለድርሻ አካላት ከተውጣጣ ብሄራዊ የደረጃ ዝግጅት ኮሚቴ ጋር በጋራ ነው።

የግብርና፣ ምግብና የግንባታው ኢንደስትሪውን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የፀደቁት ደረጃዎች በአገሪቱ በሚቀየሱ ብሄራዊ ፖሊሲዎች እንደ መመሪያ ያገለግላሉ።

ኤጀንሲው ዛሬ በሰጠው መግለጫ የፀደቁት ደረጃዎች የዜጎችን ሁለንተናዊ ጤናና ጥቅም ለመጠበቅ የሚያስችል የምርት ጥራት ከማረጋገጥ ባሻገር በተለይ የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ውጤታማነት ለማሳደግና የንግድ የተወዳዳሪነትን አቅም ለማጎልበት ያግዛሉ ተብሏል። 

በኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጅሩ፣ እንደለጹት፣ ዛሬ በአራት ዘርፎች ጸድቀው ይፋ የሆኑት 168 ደረጃዎች የምርቶችን ጥራት ለማሳደግ፣ ጥራትን ለመቆጣጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማበረታታት ዓይነተኛ ሚና አላቸው።

በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጅነሪንግ 82 አዲስ፣ 2 የተከለሱና 35 በማስቀጠል በዘርፉ በድምሩ 119 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ማጽደቁን አስታውቀዋል።

በግብርና ምግብ ደረጃ በኩል 11 አዲስ፣ 24 የተከለሰና 11 በማስቀጠል በድምሩ 46 ደረጃዎች የፀደቁ ሲሆን በኤሌክትሮሜካኒካል ዘርፍ ደግሞ 1 አዲስ 1 በክለሳ በድምሩ 2 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ወጥተዋል።

በተለይ “Standards for standards – Guideline for the use of national standards in public policy ” በሚል ይፋ የሆነው የደረጃዎች ዝርዝር የቁጥጥር ስራን፣ ጥናትና ምርምርን ፣ የህግ አሰተያየት ለመስጠትና መሰል ተግባራት  እንደ  ማጣቀሻ የሚያገለግል መረጃንም አካቶ ይዟል።

በአገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል የተባለ የተሽከርካሪዎች ፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ደረጃም መፅደቁን ኤጀንሲው አመልክቷል።

መሳሪያው በተሽከርካሪ አካል ላይ በመገጠም ተሽከርካሪው በምን ያህል ፍጥነት መሄድ እንዳለበት የፍጥነት ወሰንን የሚቆጣጠር ነው ተብሏል።