የክልሉ ሕዝብ የዴሞክራሲና የፍትህ ችግሮች በአገራዊው ለውጥ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲፈቱ አሕፓ ጠየቀ

60

ሰመራ ሚያዚያ 1/2011 የክልሉ ሕዝብ  የዴሞክራሲና የፍትህ ችግሮች በአገራዊው ለውጥ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲፈቱ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ(አሕፓ) ጠየቀ።

ፓርቲው በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የአቋም መግለጫ ዛሬ አውጥቷል።

ፓርቲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በአገር ደረጃ የተጀመረው ለውጥ የክልሉ ሕዝብ ያሉበትን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት በሚያስችል መልኩ መተግበር ያስፈልጋል።

በክልሉ ባለፉት ወራት ለውጡን ለማራመድ የተደረገው ጥረት ውስንነት ያለበት፣ አቃፊ ያልሆነና አገር አቀፍ ለውጡ በሚመራበት የመደመር እሳቤን ያልተከተለ መሆኑን አመልክቷል።

የክልሉ ገዢ ፓርቲ በወረዳዎች እያደረገ ያለው ሪፎርም ሕዝብን ያላሳተፈ፤ ከጠባብነትና ጎሰኝነት እንዲሁም ቡድንተኝነትና ከሙስና ባልጸዳ መልኩ የተካሄደ ባለመሆኑ እንዲስተካከል ጠይቋል።

በመሆኑም  ሪፎርሙ ሁሉንም ባሳተፈ መንገድ አንዲካሄድና ያገባኛል የሚሉ ወገኖችን በማሳተፍ እንዲከናወን ፓርቲው አሳስቧል።

በክልሉ ሰላም፣ልማት፣ ዴሞክራሲና ፍትህ እንዲሰፍን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ምሁራን፣የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር መድረክ እንዲዘጋጅም ሐሳብ አቅርቧል።

አሕፓ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በቅርቡ ከውጭ ከገቡና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም