የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች የጋራ የሠላም ኮንፈረንስ ተጀመረ

181

አሶሳ ሚያዚያ 1/2011 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና  የኦሮሚያ ወንድማማች ህዝቦች ለዘመናት ያዳበሩትን የጋራ ሠላም በለውጥ እና በመደመር ስሜት እንዲያስቀጥሉ ተጠየቀ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የኦሮሚያ ክልሎች የማጠቃለያ የጋራ የሠላም ኮንፈረንስ ዛሬ ረፋዱ ላይ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የሠላም ኮንፈረንሱን በንግግር ያስጀመሩት  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደተናገሩት ሁለቱ ህዝቦች በቋንቋ እና ባህል ቢለያዩም በኢትዮጵያዊነት የተገነባ አብሮነት ያላቸው ናቸው፡፡

ሃገራቸው  በሚያጋጥማትን ችግሮች ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ በመቆም መፍትሄ በማምጣት እንደሚታወቁ ገልጸዋል፡፡

ይህ አንድነት ያልተመቻቸውና ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ የፖለቲካ ነጋዴዎች በየጊዜው አጃንዳ በመቅረጽ በመካከላቸው ልዩነት ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡

በክልሎቹ አጎራባች አካባቢ በነበረው ችግር በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው " ችግሮችን በማለፍ አሁን ባለበት ሠላም ደርሰዋል "ብለዋል፡፡

ክልሉ ከደቡብ ቀጥሎ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች መገኛ እንደሆነ ጠቅሰው ይህንን ብዝሃነት እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ለሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በተያዘው  ዓመት  በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ትምህርት መስጠት መጀመሩን   ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል፡፡

"ክልሉ ከዚህ በኋላ ዜጎች የማይፈናቀሉበት እንዲሆን እንሠራለን"  ያሉት አቶ አሻድሊ የህግ የበላይነት ለድርድር እንደማይቀርብ አስታውቀዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተደረገ ጥረት መኖሩን አመልክተው በዚህ ሂደት የኦሮሚያ ክልል መንግስት ላደረገው ድጋፍ አድንቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሎቹ ህዝቦች በለውጥ እና በመደመር እሳቤ አንድነታቸውን ማጠናከራቸው  ምቾት የማይሰጣቸውን የለውጥ አደናቃፊዎችን እንዲታገሉም ጠይቀዋል፡፡

በኮንፈረንሱ የሁለቱ ክልሎችን ታሪካዊ ትሰስር የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሁፍ እየቀረበ ይገኛል፡፡

በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ  በተሳታፊዎቸ ውይይት እንደሚደረግም ይጠበቃል፡፡

በኮንፈረንሱ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፋሪት ካሚል፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፣  አባገዳዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎችም እንግዶች እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም