በመቀሌ ከተማ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ44 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ

56

መቀሌ  ሚዝያ 1/2011 በመቀሌ ከተማ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ44 ኪሎ ሜትር አዲስ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ መጀመሩን የከተማው አስተዳደር የመሰረተ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሀብቱ መብራህቱ እንዳሉት ግንባታው አሁን በከተማው ያለውን የውስጥ ለውስጥ ጠጠር መንገድ ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል።     

የመንገዱ ግንባታ ሥራ ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው የመንገዱ መገንባት የተለያዩ የከተማዋን አካባቢዎች ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ ለመንገዱ ግንባታ 2 ቢሊዮን 500 ሺህ ብር የተመደበ ሲሆን ሥራውም በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

መንገዱ በከተማው ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከማቃለሉም በላይ ለንግድ እንቅስቃሴ መቀላጠፍ የጎላ አስተወፅኦው እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የመንገድ ግንባታው አብዛኛው የሚከናወነው ከዋና የከተማዋ ክፍል ወጣ ባለ አካባቢ መሆኑን ጠቁመው ይህም በወሰን ማስከበር የሚነሳ የገንዘብ ካሳ ጥያቄ እንዳይኖር ማድረጉን አመልክተዋል።

አንዳንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው አሁን የተጀመረው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ የብዙ ጊዜ ጥያቄያቸው እንደነበር ተናግረዋል።

በመቀሌ ከተማ ልዩ ስሙ ላጪ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ አብርሃ ካሕሳይ የመንገዱ ግንባታ ሳይሰራ በመዘግየቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ ተማሪዎች በትራንስፖርት አገልግሎት ሲቸገሩ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን የገለጹት አቶ አብርሃ መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የትራንስፖርት ችግራቸውን ከማቃለል ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን በተሻለ እንደሚያፋጥን እምነታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሀብተማርያምለገሰ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው አካባቢያቸው አቧረማ በመሆኑ እሳቸውን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ለትራኮማና ለሳንባ በሽታ ተጋልጠው መቆታቸውን ተናግሯዋል።

"የመንገዱ መገንባት ይህን የጤና ችግር ያስቀራል የሚል ተስፋ አሳድሮብኛል" ሲሉም ገልጸዋል።

የታክሲ አሽከርካሪ የሆነው ወጣት አዲስ ሕንጻ በበኩሉ "አሁን የምንገለገልበት መንገድ ጠጠር በመሆኑ ክረምት ሲመጣ ጭቃ ይይዘናል፤ ለተሳፋሪና ለእኛም ያስቸግራል" ብሏል።

እንደወጣቱ ገለጻ መንገዱ አስፓልት ባለመሆኑ የመኪና ባሌስትራና ሌሎች የውስጥ መለዋወጫ እቃዎች እንዲሰበሩና በዚህም ላላስፈላጊ ወጪ ሲዳረጉ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው የተጀመረው የአስፋልት መንገድ ከተጠናቀቀ በኋላ ይደስርባቸው የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ እንደሚያቃልልላቸው ተስፋውን ገልጿል።

የመንገድ ግንባታውተቋራጭ ወኪል ችፍ ሰርቨየር ደስታዓለም ካሕሳይ እንዳሉት፣ በሳይታችን የወሰን ማስከበር ጥያቄ የሌለበት በመሆኑ መንገዱን በጥራትና በፍጥነት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ አመለክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የአፈር ጠረጋና ቁፋሮ ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለግንባታ ሥራው የሚሆኑ ባለሙያዎችና ከባድና ቀላል ማሽነሪዎች መሟላታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም