በኢትዮጵያ በፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለው ቃጠሎ በብዝሃ ህይወት ላይ ስጋት ፈጥሯል

128

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2011 በኢትዮጵያ በፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለውን ቃጠሎ መከላከል የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት ካልተቻለ የብዝሃ ህይወት መዋቅር አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የእሳት አደጋ በሚያሰጋቸው ፓርኮች አካባቢ የእሳት አደጋ መከላከል ብርጌድ ለማቋቋም እየተሰራ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በፓርኮች የሚደርሰው የእሳት አደጋ በብዝሃ ህይወት ላይ ጫና እያሳደረ ነው።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ከ40 በላይ አጥቢ እንስሳትና ከ6 በላይ የወፍ ዝርያዎች የሚገኙበትን ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጨምሮ ትላልቅ ፓርኮች ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ እንስሳት መኖሪያቸውንና ምግባቸውን አጥተዋል።

መብረርና መራመድ የማይችሉ ህይወትና ዝርያቸው መጥፋት፣ በአይን የማይታዩና ደቂቅ አካላት መውደምና ሌሎች ተጽእኖዎች  ከባድ መሆኑን ይናገራሉ።

እንስሳት ምግብና የመኖሪያ አካባቢ ፍለጋ ወደ ሌላ አካባቢ በሚሰደዱበት ወቅት አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

በመሆኑም በቀጣይ የእሳት አደጋን ቀድሞ በመከላከልና ሲከሰት ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት በእንስሳት እና እጽዋት መኖር ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መቀነስ የሚያስችል ዝግጁነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ቲመር በበኩላቸው  በበጋ ወቅት ፓርኮች ለእሳት አደጋ ተጋላጭነታቸው እንደሚጨምር ጠቁመዋል።

የእሳት አደጋው በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት ሊነሳ እንደሚችል ጠቅሰው አብዛኛውን ጊዜ የሚነሳው ከሰው ጋር ግንኙነት ባላቸው ምክንያቶች መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ባለስልጣኑ በሁሉም ጥብቅ ቦታዎች በአንድ ጊዜ መተግበር ባይቻልም በተመረጡና የእሳት አደጋ በሚያሰጋቸው አካባቢዎች የእሳት አደጋ መከላከል ብርጌድ ለማቋቋም እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በቅድመ መከላከል በኩልም ስለ እሳት አደጋ ህብረተሰቡን የማስተማር ተግባር ማጠናከር፣ የግጦሽ ቦታዎች አስተዳደር፣ ህብረተሰቡን ከፓርኮች በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ማድረግና ሌሎች ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

የሚሰሩ መንገዶችም የእሳት አደጋ ሲነሳ ፈጥኖ ለመድረስ የሚያስችሉ መሆን እንዳለባቸው አንስተዋል።

በመሆኑም በቀጣዩ አመት የበጋ ወቅት እሳት ሲያጋጥም በቴክኖሎጂ የታገዘ የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ዝግጅት ይኖራል ብለዋል።

በሚፈጠረው የእሳት አደጋ ብዝሃ ህይወት ሙሉ ለሙሉ መጥፋትና መልሶ ለማገገም እስከ 20 አመት ሊወስድ እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ በክልልና በፌዴራል የሚተዳደሩ 27 ብሔራዊ ፓርኮችና ሌሎች የጥበቃ ቦታዎች እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም