በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል በኩርሙክ ወረዳ የተገነባው ጤና ጣቢያ ሥራ እንዲጀምር ነዋሪዎች ጠየቁ

114

አሶሳ መጋቢት  30/2011 በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ ግንባታው የተጠናቀቀው ጤና ጣቢያ በአፋጣኝ አገልግሎት እንዲሰጥ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

በወረዳው በዱል ሽታሎ ቀበሌ  ከ5 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ የተገነባው ጤና ጣቢያ መጋቢት 28/2011 ዓ.ም ተመርቋል፡፡

በምረቃው ወቅት የአከባቢው ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት በ2007 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ይኸው ጤና ጣቢያ ሳይጠናቀቅ ሲጓተት ቆይቷል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሚልጋን ጣሂር  በሰጡት አስተያየት በቀበሌው የተገነባው ጤና ጣቢያ ለዓመታት ከተጓተተ በኋላ ለምረቃ የበቃው የረጅም ጊዜ ጥያቄቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ የጤና ማዕከል ባለመኖሩ ወደ አሶሳ ከተማ 120 ኪሎ ሜትር ህክምና አገልግሎት ፍልጋ እንደሚጓዙ የገለጹት አስተያየት ሰጪዋ ይህም ለእንግልት እና ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጤና ጣቢያው በአካባቢው መገንባቱ በተለይም ወላድ እናቶችን እና ህጻናትን ከጉዳት  ለመታደግ እንደሚረዳ  ጠቁመዋል፡፡

ጤና ጣቢያ በቂ ባለሙያና የመገልገያ ቁሳቁስ ተሟልቶለት  በፍጥነት ሥራ እንዲጀምር ጠይቀዋል፡፡

አዲስ የተገነባው ጤና ጣቢያ የሚያስፈልጉት የውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ተደራጅተውላት ፈጥኖ ስራ እንዲጀምር የጠየቁት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ  አቶ ጣሂር አህመድ ናቸው፡፡ 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ ጤና ጣቢያውን በአፋጣኝ ለማስጀመር ቢሮው 100 ሺህ ብር ግምት ያለው መድኃኒት ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ጤና ጣቢያው በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ድጋፋቸው እንደሚቀጥል ገልጸው ወረዳው ተገቢውን የሰው ኃይል አሟልቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ህብረተሰቡ በተለይም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ በሽታን አስቀድሞ በመከላከልና ጤናውን መጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ሽፋኑ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ለጤና ጣቢያው የክልሉ መንግስት አስፈላውን እንደሚደረግ ተናግረው ህብረተሰቡ እና የጤና ባለሙያዎች የጤና ተቋሙን በመንከባከብ የሚጠበቀውን ያህል አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ጤና ጣቢያው በአካባቢው ለሚገኙ እስከ 20 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም