የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጠው መግለጫ

96
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ በሞያሌ ከተማ በሚያዝያ 28/2010 ዓ.ም በተደራጀና በህቡእ ዝግጅት በተደረገበት የጥፋት ተልዕኮ በሁለት ጎራዎች የታጠቁ  ኃይሎች መካከል ማህበረሰብን ኢላማ ያደረገ በመጠኑም ሰፋ ያለ ግጭት ተከስቶ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡በዚህ ግጭት የዜጎች ህይወት ጠፍቷል የመቁሰል አደጋም ደርሷል፡፡ በመላ ሀገሪቱ መንግስት እና የጸጥታ ኃይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እያካሄዱ ባሉት ተከታታይ ስራና ጥረት ሰላምና መረጋጋት  እየሰፈነ ባለበት በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ መካከል ግጭት እንዲፈጠርና ያለ መረጋጋት እንዲሰፍን በሚሰሩ የሁከትና ብጥብጥ ኃይሎች ምክንያት ለደረሰው የዜጎች ህይወት መጥፋት ኮማንድ ፖስቱ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡ በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉና ከጀርባ ሆነው ድርጊቱን ሲመሩ የነበሩ አጥፊዎችን የመለየትና የማጣራት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ሀይሎች ግጭቱን ያስቆሙት ሲሆን ሁኔታዎቹም በመረጋጋት ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ህገ-ወጥ የጦር መሳርያ ዝውውር በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ተገንዝቧል፡፡ እስከ አሁን የጸጥታ ኃይሎች ባካሄዱት ጥብቅ ክትትልና በህብረተሰቡ ጥቆማ በሚያዝያ ወር 2010 ዓ/ም ብቻ 142 ክላሽ፣88 ሽጉጥ፣17 የኋላ ቀር መሳርያዎች ከበርካታ ተተኳሾች  ጋር እንዲሁም 11 የእጅ ቦምቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ይህ ህገወጥ የጦር መሳሪያ በሞያሌ ከተማም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶችና ለሚደርሰው ጉዳት ስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ በመሆኑም በሞያሌ ከተማ የጸጥታ ኃይሉ ከመንግስት በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ትጥቅ የማስፈታት ስራ እያከናወነ ሲሆን አስፈላጊው ጥናት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ሁሉ የተጠናከረ ትጥቅ የማስፈታት እርምጃ የሚቀጥል መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ያስገነዝባል፡፡ ህጋዊና ለስራም ሆነ ለአካባቢ ጥበቃ የሚውል ትጥቅ ያላቸው ዜጎችም ትጥቃቸው ለማንኛውም ግጭት መንስኤና ለህገ-ወጥ ድርጊት አገልግሎት እንዳይውል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኮማንድ ፖስቱ ያሳስባል፡፡ በመጨረሻም ሕብረተሰቡ ሠላሙን ከሚያናጉ ማንኛውም ኃይሎች ሴራና የጥፋት ድርጊት ራሱን በመጠበቅና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ በመስራት የከተማውን ብሎም የአካባቢውን ሠላም የማስጠበቅ ስራ እንዲቀጥል ኮማንድ ፖስቱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም