የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ግብርናውን በምርምር ማዘመን እንደሚገባ ተጠቆመ

199

ነቀምት መጋቢት 30/2011 በአገሪቱ የአርሱ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ግብርናን የማዘመን ሥራ መስራት እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡

” በኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ  የቴክኖሎጂ፣ የፖሊሲና  የግኝቶች ሚና ”  በሚል ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት መኖና ሥነ ምግብ ባለሙያ ፕሮፌሰር አዱኛ ቶሌራ እንዳሉት አገሪቱ ለሰብልና ለእንስሳት እርባታ ምቹ ብትሆንም በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አይደለችም፡፡

በአገሪቱ የግብርና አመራረት ከልማዳዊ የአሠራር ዘዴ ብዙም እንዳልተላቀቀ የተናገሩት ፕሮፌሰሩ  የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያሉ ውስንነቶች የሕዝቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንቅፋት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በየደረጃው በሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች የአርሶ አደሩን አቅም ማጎልበትና በዩኒቨርሲቲዎችና በግብርና  ምርምር ማዕከላት የተገኙ የምርምር ውጤቶችን መጠቀም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች  አርሶ አደሮችን በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እስኪያደርጉ ድረስ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ በማካሄድ ግብርናውን ማዘመን እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

የደምበሊ የወተት ላም እርባታና የወተት ተዋጽኦ ማምረቻ ባለቤት ዶክተር ዓለምፀሐይ ተስፋ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ በአገሪቱ የእንስሳት እርባታ ውጤታማ እንዳይሆን የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የእንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆን፣ የመኖ እጥረት፣ የእንስሳትን ጤና አለመጠበቅ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

“የእንስሳት እርባታን በማሻሻል አገሪቱ ከእንስሳት ሀብት ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ  የመንግስት ፖሊሲ፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ የመኖ አምራቾችና አርሶ አደሩ በጋራ ተነጋግረው መፍትሄ መፈልግ ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም አገሪቱ የምታመርተው የእንስሳት ምርት ከጎረቤት አገሮች ኬንያና ሱዳን ያነሰ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይ በዘርፉ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ወደአርሶ አደሩ ወርደው ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ በማከናወን ግብርናውን ማዘመንና በዚህም ህብረተሰቡንና ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

“የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ችግር መፍታት ስላለባቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የእርሻ ምርምር ማዕከላት በምርምር የተገኙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀምባቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል” ያሉት ደግሞ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሻምቡ ካምፓስ ዲን ዶክተር ካሳሁን ጉርሜሳ ናቸው፡

ምሁራን ችግር ፈቺ ምርምር በማካሄድና አርሶ አደሩን ከቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተዋወቅ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር በሻቱ ፈረደ በበኩላቸው በኮንፍረንሱ ላይ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ  በሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ላይ የተካሄዱ 45 ጥናታዊ ጽሁፎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

መድረኩ በጥናትና ምርምር የተገኙ ቴክኖሎጂዎችን በውይይት በማዳበር አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከባኩ ግብርና ምርምር ማዕከልና መሰል የምርምር ተቋማት ተጋብዘው የመጡ ከ300 በላይ ምሁራን ተገኝተዋል ነው።