ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያዊው ኢንቨስተር የክብር ዜግነት ሰጠች

92

መጋቢት 30/2011 ከረጅም ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት  በኋላ አንፃራዊ የሰላም ጉዞ የጀመረችው ደቡብ ሱዳን አቶ አይሸሽም ተካ ለተባሉ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተር የክብር ዜግነት ሰጠች።

ደቡብ ሱዳን ከሰሞኑ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያዊው ኢንቨስተር የክብር ዜግነት መስጠቷ ታውቋል።

በደቡብ ሱዳን ታሪክ አቶ አይሸሹም ተካ የክብር ዜግነት የተሰጣቸው ብቸኛ እና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ኢንሸስተር መሆናቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ከሰሞኑ በተካሄደው "የደቡብ ሱዳን ታላቁ ሩጫ" ዝግጅት ጋር ተያይዞ  በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፤ ለኢትዮጵያዊው ኢንቨስተር  የክብር ዜግነት ዕውቅና የተሰጣቸው፤ በሃገሪቱ ለተገኘው ሰላም፣ ብሄራዊ አንድነት እና የልማት ጉዞ በግላቸው የተጫወቱትን ሚና እና አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑ ተገልጿል።

በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር "አቶ አይሸሽም ተካ እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ የደቡብ ሱዳን ህዝብ በአስቸጋሪ ቀውስ ውስጥ በገባበት ጊዜ ባላቸው አቅም ሁሉ ከፊት እና ከጀርባ ሆነው በታሪክ የማይዘነጋ ድጋፍ ያደረጉ ዕውነተኛ ወንድማችን ናቸው" ብለዋል።

"የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ህዝብ ለደረሰበት ተስፋ ሰጪ የሰላም እና የለውጥ ምዕራፍ የወንድማችን አቶ አይሸሽም ተምሳሌታዊ አሻራ በትውልዱ እየታወሰ እንዲዘልቅ የመጀመሪያው የክብር ዜጋችን እንዲሆኑ መንግስት በታላቅ ደስታ ወስኗል" ብለዋል።

አቶ አይሸሽም ተካ በደቡብ ሱዳን በተለያዩ የልማት መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተር ሲሆኑ፤ "የደቡብ ሱዳን ታላቁ ሩጫ" እኤአ ከ2017 ጀምሮ በመሪ አዘጋጅነት የህዝብ ለህዝብ ሰላማዊ ግንኙነቱ ትርጉም ባለው ደረጃ እንዲሻሻል ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል።

በተጨማሪ አቶ አይሽሽም በተለያዩ የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች ላይ በመሰማራት የደቡብ ሱዳን በርካታ ወጣቶች በስራ ዕድል ፈጠራ መርሃግብር እንዲታቀፉ፤ በበጎ ፈቃደኝነት የፋይናንስ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፤ የደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ ዘርፈብዙ ግንኙነት እንዲጠናከር ብርቱ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም