መንግስት የከተማ ግብርና ፖሊሲ ቀርፆ ሊተገብር ይገባል-የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት

91
አዲስ አበባ ግንቦት 25/2010 በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎችን የድህነት ሁኔታ ለማሻሻል ያግዝ ዘንድ መንግስት የከተማ ግብርና ፖሊሲን ቀርፆ መተግበር እንዳለበት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አሳሰበ። ኢንስቲትዩቱ ለውጤታማ የከተማ ግብርና የሚያስፈልጉ ዘርፎችን በጥናት በመለየት ለመንግስት ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል። ኢንስቲትዩቱ 'ሴንተር ፎር ዲቨሎፕመንት ኤንድ ካፓሲቲ ቢዩልዲንግ' ከተባለ ሀገር በቀል የስልጠናና ማማከር ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በከተማ ግብርና ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ አካሄዷል። የከተማ ግብርና ልማት በአፍሪካ ሀገራት የነዋሪዎችን ህይወት በማሻሻል ትልቅ ሚና እየተጫወተ ሲሆን በተለይም በኬንያዋ ናይሮቢ ዘርፉ የመዲናዋ ነዋሪዎችን 50 በመቶ ገቢ ይሸፍናል ተብሏል። ሴራሊዮን እና ቦርኪናፋሶም በአፍሪካ የከተማ ግብርና የሚካሄድባቸው ግንባር ቀደም ሀገራት ናቸው። በአውሮፓ የእንግሊዟ ዋና ከተማ ለንደን፤ በኢሲያ ደግሞ የሲንጋፖር ከተሞች የከተማ ግብርና ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ መሆናቸውም ይነገራል። በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ከ20 በመቶ አይበልጥም፤ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ከተሞች ከአምስት በመቶ በሚበልጥ ፈጣን እድገት በመስፋፋት ላይ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ግብርና ምርመር ኢንስቲትዩት የተገኘ መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እንዳሉት፤ "በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች በገጠር ከሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች በባሰ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ"። በመሆኑም መንግስት በፍጥነት እያደገ ያለውን የከተሞች መስፋፋት በመረዳት የከተማ ግብርና ፖሊሲ ተግባራዊ ካላደረገ ችግሩ ከዚህ የከፋ ይሆናል ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ በከተሞች መስፋፋት ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎችን፣ መሰማራት የሚፈልጉበትን የስራ ዘርፍ እና እንደ ከተሞቹ ነባራዊ ሁኔታ ለከተማ ግብርና የሚያስፈልጉ ዘርፎችን በጥናት አስደግፎ ለመንግስት ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል። የከተማ ግብርና ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም በጥናት የተደገፈ ሰነድ ለመንግስት ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቅሰዋል። የከተማ ግብርና የከተማ ነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅም ከማሳደግም ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው። የ'ሴንተር ፎር ዲቨሎፕመንት ኤንድ ካፓሲቲ ቢዩልዲንግ' ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አድነው በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል በረክ ወረዳ የተጀመረው የከተማ ግብርና የነዋሪዎችን ህይወት የሚቀይር ስለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ነው ብለዋል። የመንግስት አመራሮችና ግለሰቦች ለዘርፉ የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ቢሆንም፤ በአግባቡ ከተሰራበት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በበረክ ወረዳ በዶሮ እርባታና ጓሮ አትክልት የተሰማሩ 65 ተሳታፊዎች ምስክር ናቸው ሲሉም አመልክተዋል። ከተሞች በፍጥነት እየተስፋፉ ባሉ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በተለይ "በከተሞች መስፋፋት ምክንያት ስለሚፈናቀሉ በፍጥነት ወደ ስራ ካልገቡ ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ በተግባር አይተናል" ብለዋል። በከተሞች መስፋፋት ለሚፈናቀሉም ሆነ ከገጠር ወደ ከተማ ለሚፈልሱ ዜጎች ግብርና የለመዱት በመሆኑ የከተማ ግብርና ማስፋፋት ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም