እየተስተዋለ ላለው የኤሌክትሪክ መቋረጥ ችግር መንስኤው የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለማሻሻል የተጀመረው መርሃ ግብር ነው ተባለ

246

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የኤሌክትሪክ መቋረጥና መቆራረጥ ችግር ለመፍታት የኤሌክትሪክ መስመሮችን የማሻሻል ተግባር መጀመሩን ኤክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

ሰሞኑን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋለው የኤሌክትሪክ መቋረጥና መቆራረጥ ችግር መንስኤውም ይኸው የኤሌክትሪክ መስመሮችን የማሻሻል ተግባር እንደሆነ ተጠቅሷል።

አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በስልክ በጠሱት ጥቆማ በተለይ በዚህ ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ መቆራረጥና መቋረጥ ችግር እየገጠማቸው ነው።

ችግሩ በተለይ በመገናኛ፣ ፒያሳ፣ ጀሞና አካባቢው የከፋ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሰጠው ምላሽ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰተውን የኤሌክትሪክ መቋረጥና መቆራረጥ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

ሰሞኑን ለተፈጠረው የኤሌክትሪክ መቆራረጥና መቋረጥ ምክንያቱም በአብዛኛው ይኸው ተግባር መሆኑን  የአገልግሎቱ የኮሙዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ አስታወቀዋል።

በመሆኑም ይህ የተጀመረው ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የከተማዋ ነዋሪ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፈዋል። 

አሁን እየተካሄደ ያለው የመስመር ማሻሻያ መርሃ ግብር አሮጌውን ምሰሶ በአዲስ የመቀየርና ኔትወርኩን የማሻሻል ስራን የሚያካትት መሆኑንም  አቶ በቀለ ገልፀዋል።

እንዲያም ሆኖ ግን ስራው የሚካሄደው  በእቅድ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቋረጥባቸው ቦታዎች ከ72 ሰዓት በፊት በመገናኛ ብዙሃን የሚገለፅ በመሆኑ ህብረተሰቡም በዚሁ መሰረት ቅድመ ጥንቃቄ ያደርግ ዘንድ መክረዋል።

በየአካባቢው የሚከናወነው የማሻሻያ ተግባር የሚወስደው ጊዜ ከ 8እስከ 10 ሰዓታ መሆኑን የጠቀሱት አቶ በቀለ የኤሌክትሪክ መቋረጥ ለብዙ ሰዓት የሚቆየው ግን በመስመሩ ላይ ብልሽት ሲያጋጥም መሆኑን ተናግረዋል።

የተጀመረው የኤሌክትሪክ መስመር ማሻሻያ በከተማዋ የሚከሰተውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት አቶ በቀለ ማሻሻያው እስኪጠናቀቅ ድረስ ለሚከሰተው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የከተማዋ ነዋሪ በትዕግስት እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል።