የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርተኞችና አመራሮች በመቀሌ ችግኞች ተከሉ

57

መቀሌ መጋቢት 29/2011 በአገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር የተሳተፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርተኞችና አመራሮች በኩይሃ መለስ ዜናዊ አመራር የስልጠና ማዕከል ቅጥር ግቢ የችግኝ ተከላ አካሄዱ።

የችግኝ ተከላው በትግራይ ክልል ሕዝብና መንግሥት ለተደረገላቸው መስተንግዶ ለማስታወሻ እንዲሆን ታስቦ መከናወኑን የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።

በመርሐ ግብሩ የተሳተፉት 500 ስፖርተኞችና አመራሮች በነፍስ ወከፍ ችግኝ ተክለዋል።

የችግኝ ተከላ ካከናወኑ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አያሌው ዓለሙ "ላከበረን ሕዝብና መንግሥት ለማስታወስ ይረዳናል ያልነው የችግኝ ተከላ አከናውነናል" ብለዋል።

"ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው" ያሉት ተሳታፊው፣ኅብረተሰብ የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት እንዲሆን ጠይቀዋል።

በቮሊ ቦል ጨዋታ ተሳታፊ የነበረው ወጣት በረከት ምትኩ በበኩሉ "በመንገድ ላይ አሞኝ በኩይሃ ሆስፒታል በጤና ባለሙያዎች በተደረገልኝ የህክምና ድጋፍ ሕይወቴ ሊተርፍ ችሏል" ብሏል።

በኩይሃ መለስ ዜናዊ አመራር የስልጠና ማዕከል ቅጥር ግቢ ችግኝ የተከልኩት ጤናና ፍቅር ለሰጡኝ የጤና ባለሙያዎችና ለሕዝቡ ያለኝን ፍቅር ለመግለፅ ነው ሲል ተናግሯል።

ወጣቱ ከጥላቻ ወጥቶ የሰላም፣የፍቅርና የአንድነት መንገድን እንዲከተል መልእክቱን አስተላልፏል።

በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ የተተከለውን ችግኝ በመንከባከብ ለእናንተ ያለንን ፍቅር እንገልጻለን ብለዋል።

የደቡብ ክልል ስፖርተኞችና አመራሮች የሰማዕታትንና ሌሎች ታሪካዊ ቦታዎችን ጎብኝተዋል።

ከመጋቢት 14 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2011በመቀሌ ከተማ በተካሄደው አገር አቀፉ የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም