መንግስት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ተጠየቀ

150

ደሴ መጋቢት28/2011 ህዝቡ ሰላምና ደህንነቱ ተጠብቆ ያለስጋት የሚኖርበት ሁኔታ እንዲፈጠር መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

ነዋሪዎቹ "በመንግስት አላስፈላጊ ትዕግስት ህዝብ መሞት የለበትም" በሚል  ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ  አካሂደዋል፡፡

"የህግ የበላይነት ይከበር፣ መንግስት በጥፋተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይውሰድ፣ በጸጥታ ምክንያት የሚሞቱ ዜጎች ደም ደማችን ነው፣ ታጥቀው ህዝብን የሚገድሉ ቡድኖች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ" የሚሉ መልእክቶች በሰልፈኞቹ ተላልፈዋል ።

ነዋሪዎቹ ከሰልፉ በኋላም በሆጤ ስታዲዮም በመሰብሰብ ከሚመለከታቸው የክልል ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል

በከተማው የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱ ይማም በወቅቱ እንደገለፁት በመንግስት አላስፈላጊ ትግዕስት ብጥብጥና ሁከት ተበራክቷል፡፡

"በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚስተዋሉ የሰላም እጦት፣ የህይወት ጥፋት፣ የመፈናቀል፣ የአካል ጉዳትና ንብረት ውድመት ህዝቡ  እንዳይረጋጋና እንዲሰጋ አድርጎታል" ብለዋል ።

ሰሞኑን በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በተከሰተው የጸጥታ ችግርም ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸው መጥፋቱንና ይህም  ለስጋት እንደዳረጋቸው  ጠቅሰዋል ።

"መንግሰት አስቀድሞ መረጃዎች ቢደርሱትም እርምጃ ባለመውሰዱ ህዝቡን ቅሬታ ውስጥ ገብቷል" ብለዋል ።

ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት መንግስት አመላካች ጉዳዮችን በማጥናት የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ሌላዉ የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሀብታሙ ልዑል "መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመቆራኘት ሰለማችንን መጠበቅ ይኖርበታል" ብለዋል፡፡

በለውጡ የተገኘው  ሰላም፣ አንድነትና መቻቻል ለማስቀጠል  መንግስት ከጎናችን ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

"የሚፈጠሩ ብጥብጦችን ለማብረድና ይቅርታ መጠየቅ ሳይሆን ቅድሚያ መስራትም ያስፈልጋል" ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

"በዛሬው ሰልፍ ሰዎች እንዳይጎዱና ንብረት እንዳይወድም ወጣቱ ሲሰራ ነበር" ያሉት አቶ ሀብታሙ የተዘጉ መንገዶችም እንዲከፈቱ ወጣቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል ።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን  የጸጥታ ችግር የፈጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረው

ህዝቡ አጥፊዎችን አሳልፎ በመስጠት የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

"በሰልፉ ድንጋይ ሳይወረወር፣ ሰውና ንብረት ሳይጎዳ በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረገው የደሴ ወጣቶችና አጠቃላይ ህዝብ ምስጋና  ይገባዋል" ብለዋል ፡፡

አቃቤ ህጉ በወቅቱ እንዳሉት ደሴ የመቻቻል፣ የአብሮነትና የሰላም ወዳድ ህዝብ መኖሪያ መሆኑን በተግባር ማስመስከር ችሏል ፡፡

"የክልሉን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባራችን ነው"ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ናቸው፡፡

ወጣቱ በጥቅመኞች ሳይታለል በአስተውሎት ከአመራሩ ጋር በመስራት የጀመረውን የሰላም ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽነሩ  አመልክተዋል፡፡

ሰሞኑን በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ደዌ ሀረዋ ወረዳ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ለአራት ሰዎች ሕይወት መጥፋትና ለአካል ጉዳት መዳረግ  ምክንያት እንደሆነ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም