በክልሉ ለኢንዱስትሪ የሚውል በቂ ምርት በጥራት እንዲመረት አመራሩ ኃላፊነቱ ሊወጣ ይገባል---ዶክተር አምባቸው መኮንን

91

ባህርዳር  መጋቢት 28/7/2011 በአማራ ክልል በቀጣዩ የመኸር ወቅት ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል በቂ ምርት በጥራት እንዲመረት አመራሩ ኃላፊነቱን በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር  አምባቸው መኮንን አሳሰቡ።

የ2011/2012 የምርት ዘመን የሰብል ልማት ዕቅድ ላይ የሚመክር መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ እንደገለጹት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው  መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን የግብርና ምርትን ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።

የተሻሻሉ የግብርና አሰራር ዘዴዎችን በመተግበር ሁላችንም ዕቅዱን ለማሳካት መረባረብ ያስፈልጋል።

" በተለይም እየተስፋፋ ለመጣው ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ምርት በጥራትና በብዛት ማቅረብ ግድ በመሆኑ ከወዲሁ ይህን እያሰቡ መስራት ይገባል" ብለዋል፡፡

" አርሶ አደሩ የመኽር እርሻ እንቅስቃሴ የጀመረበት ወቅት ነው " ያሉት ዶክተር አምባቸው  ከልማዳዊ አሰራር እንዲላቀቅ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ለዚህም የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችም በወቅቱ ለአርሶአደሩ በማቅረብና ሙያዊ እገዛ በማድረግ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ስራውን እየገመገመ መምራት አለበት "ብለዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ በበኩላቸው ባለፈው የመኸር ወቅት ከለማው መሬት 103 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት መገኘቱን አስታውሰዋል።

በቀጣዩ የምርት ዘመን በመኽር ከሚለማው አራት ሚሊዮን 400ሺህ  ሄክታር መሬት 120 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዷል፡፡

ዶክተር ሰሎሞን እንዳመለከቱት ከሚለማው መሬት ውስጥም ግማሽ ያህሉ በተሻሻለ አሰራር በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የማሳ መረጣና የእርሻ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

ከሚመረተውም  ግማሽ ያህሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እንዲሆን ነው የታሰበው፡፡

ለዚህም ምርጥ ዘር እና  ማዳበሪያ  በወቅቱ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤  ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በመጠቀም ባለፈው ዓመት በሄክታር 22 ነጥብ 8 ኩንታል አማካኝ የሰብል ምርታማነትን ወደ 26 ነጥብ 8 በመቶ እንደሚያሳድገውም አመላክተዋል።

ድርቅ በሚያጠቃቸውና በቂ እርጥበት በሌለባቸው አካባቢዎችም የዕርጥበት ዕቀባ ስራ አርሶ አደሩ እንዲሰራና ፈጥነው የሚደርሱ የሰብል ዘሮች እንዲጠቀም ይደረጋል፡፡

ለዚህም ቀደም ሲል በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ለአርሶ አደሩ በሰብል ምርታማነት ላይ ያተኮረ ስልጠና  ተሰጥቷል።

" ቀደም ሲል በኩታገጠም የጀመርነውን አሰራር አጠናክረን እንቀጥላለን "  ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊና በዋግህምራ ዞን የጋዝጊብላ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃብቱ እሸቴ ናቸው።።

አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ  የውሃ ማሰባሰብ ስራን አርሶ አደሩ እንዲያከናውንና ግብዓትን ተጠቅሞ እንዲያለማ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል።     

በሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳኦሮሞ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በጋሻው ጠጉ በበኩላቸው በዘመኑ ምርታማነትን ለማሳደግ  እያንዳንዱ አርሶ አደር በቂ የማዳበሪያ ግብዓት ተጠቅሞ እንዲያለማ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ለ2 ቀናት በሚቆየው የምክክር  መድረኩ ከክልል እስከ ወረዳ ደረጃ የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ሌሎችም አካላት እየተሰተፉ  ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም