በጤና ተቋማት የህክምና መሳሪያዎች ቁጥጥርና አያያዝ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለፀ

122
አዲስ አበባ ግንቦት 25/2010  በጤና ተቋማት የህክምና መሳሪያዎች  ቁጥጥርና አያያዝ ከለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየተሻሻለ መምጣቱን የአዲስ አበባ ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በመዲናው በሚገኙ 1 ሺ 135 የጤና ተቋማት ላይ ባካሄደው የህክምና መሳሪያዎች ፍተሻና ቁጥጥር ሥራ 1 ሺ 043 የሚሆኑት የህክምና መሳሪያዎች  ቁጥጥርና አያያዛቸው ጥሩ መሆኑን ገልጿል። የባለስልጣኑ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ቁጥጥር ንዑስ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ገረሱ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ 117 ወረዳዎች ላይ በሚገኙ ክሊኒኮችና  ሆስፒታሎች ላይ የህክምና መሳሪያዎች ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጓል። በመሆኑም ከጤና ጣቢያዎች ጀምሮ እስከ  ሆስፒታሎች  በተደረገው የህክምና መሰሪያዎች የጽዳትና የእቃ አያያዝ የቁጥጥርና የፍተሻ ሥራ ከለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየተሻሻለ መምጣቱን ያመላከተ መሆኑን ነው የገለፁት። የስራ ሂደት አስተባባሪው አቶ ጥላሁን፤ ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናው ከ85 በመቶ በላይ በሚሆኑ የጤና ተቋማት ላይ  የቁጥጥር  ሥራ እንደተሰራ ገልፀው ቀሪዎቹ አዳዲስ የተከፈቱ በመሆናቸው እሰከ በጀት ዓመቱ ማብቂያ ድረስ የቁጥጥርና የፍተሻ ሥራ እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት። ባለስልጣኑ በመዲናው በሚገኙ 1ሺ 135 የጤና ተቋማት ባካሄደው የህክምና መሳሪያዎች ፍተሻና ቁጥጥር ሥራ 1ሺ 043 የሚሆኑት የህክምና መሳሪያዎች  ቁጥጥርና አያያዛቸው ጥሩ ሊባል የሚችል መሆኑን የገለፁት አስተባባሪው 92 የሚደርሱት ግን መስፈርቶቹን የማያሟሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። በመሆኑም ባለስልጣኑ መስፈርቱን ባላሟሉት  92 የጤና ተቋማት ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ እገዳ የሚያደርስ ውሳኔ ማስተላለፉን ነው አስረግጠው የተናገሩት። ባለስልጣኑ በጤና ተቋማት ላይ የሚያደርገውን የክትትልና የቁጥጥር ስራ በተሟላ መልኩ እንዳይሰጥ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የባለሙያ እጥረት እንዳለም አቶ ጥላሁን ገልፀዋል። የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 661/2009  እንደሚደነግገው ማንኛውም ጤና ነክ ቁጥጥር የሚደረግበት የጤና ተቋም በአስፈጻሚ አካሉ የወጡ የጤና አጠባበቅ ደረጃዎችን ማሟላት አለበት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም