የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ገጽታና የማሻሻያው አስፈላጊነት

833

በቁምልኝ አያሌው እና በቀበኔሳ ገቢሳ

የልማታዊ መንግስት ሞዴል በሶሻሊስታዊና ማዕከላዊ ፕላን የሚመራ የእዝ ኢኮኖሚ እና በኒዮሊበራሎቹ የነፃ ገበያ ስርዓት መካከል ያለ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚሸጋገር የልማት አቅጣጫ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ ልማታዊ መንግስት  ፈጣን ዕድገት ዋነኛ ዓላማው በማድረግ ለዚህ የሚስማሙ ስትራቴጂያዊ ስልቶችን በመቀየስ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማትን ማረጋገጥ ላይ እንደሚያተኮር በዚህ ዙሪያ ያጠኑ ምህሁራን ያስረዳሉ። 

እሴተየቨን ፔሬዝ (Esteban Pérez)  International Journal of Political Economy  በተሰኘ ጽሑፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት ልማታዊ መንግስት ማለት ሕጋዊነቱን ተጠቅሞ ልማታዊ ፖሊሲና ፕሮግራሞችን ቀርፆ በስራ ላይ በማዋል ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት የሚሰራ መንግስት ነው። ልማታዊ መንግስት የሚለው የኢኮኖሚ ሞዴል ድህነትንና ስራ አጥነትን ለማስወገድ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መሣሪያ እንደሆነም ያስቀምጣሉ።

በኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ የፖለቲካ ስርአቱን ማስተዳደር ሲጀምር በኢኮኖሚው ልማት ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ሚና በተመለከተ ለየት ያለ አስተያየት መንጸባረቅ ጀምሮ ነበር። በወቅቱ ይቀርብ የነበረው አስተያየትም የምስራቅ ኢስያ ሀገሮች ያሉበት የፖለቲካል ኢኮኖሚ  ሂደትን መሰረት ያደረገ ነበር፡፡

የኢስያ ነብሮች (Asian Tigers) በመባል የሚታወቁት (ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣…) ሀገሮች ለሰላሳ ዓመታት ያህል በልማታዊ መንግስት አቅጣጫ ባደረጉት ጥረት ፈጣን የኢኮኖሚ እና የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማድረጋቸውና ከኋላ ቀር የግብርና ልማት ወደ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እድገት መሸጋገራቸው ታይቷል፡፡ ይኸው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በቀጣይ ዓመታት በህንድ፣ በቻይናና በቬትናም በመሳሰሉት የኢስያ ሀገሮችም ተስፋፍቷል።

የልማታዊ መንግስት ሞዴልን የሚከተሉ ሀገሮች ሀገራዊ ልማትና እድገት ላይ ያተኮሩበት ምክንያት እንዳላቸውም ይነገራል፡፡

ጃፓን ልማታዊ መንግስት ሞዴል ላይ ያተኮረችበት ምክንያት በሀገሪቱ ላይ ተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ቀውስ በመከሰቱ ሲሆን፤ ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ እንዲሁም ታይዋን ከቻይና የሚሰነዘርባቸውን ዛቻና ማስፈራራት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ኢኮኖሚያቸውን አጠናክረው ለመመከት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ቻይናን በተመለከተ ስልጣን ላይ ያለው ኮሙኒስት ፓርቲ ፖለቲካዊ ህጋዊነቱን  ለማረጋገጥ ሲል የህዝቡን ሕይወት የሚለውጥ የልማት መስመር መከተልን መርጧል፡፡

እነዚህ ሀገሮች የሄዱበት መንገድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በ1983 ዓ.ም ሀገሪቱን ሲመራ የነበረው የደርግ ስርዓት ተገርስሶ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የነበረው ሂደት ሃገራችን የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለምን መከተል እንደ አማራጭ ወስዶ ነበር፡፡

በዚህ ሂደትም የኢህአዴግ መንግስት በትረ ስልጣኑን ሲረከብ የኢኮኖሚ ሂደቱ በጣም የተጎዳ፣ የመሰረተ ልማት ሁኔታው እጅግ ኋላ ቀር እና በጣም ውስን የሆነ ካፒታል እና ዜጎች ከነበሩባቸው የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመላቀቅ ይፈልግ ስለነበር ልማታዊ መንግስት ርዕዮተ አለምን መከተል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው በማለት በኢኮኖሚው ውስጥ በስፋት መሳተፍ ጀመረ።

ይሁን እንጂ የልማታዊ መንግሥት አማራጭነትን በተመለከተ ምን ያህል ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ የተሻለ አዋጭ ወይም ተገቢ ተገቢ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ምሁራን እና የፖለቲካ አካላትን ብዙ ሲያከራክር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ ሂደትም ኢትዮጵያም ዋነኛ አላማዬ ፈጣን ልማትን ማስመዝገብ ነው በማለት ብትንቀሳቀስም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተፅዕኖ ይደርስባት ነበር፡፡

በኢትዮጵያም የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምስረታ ውጤታማ የሆኑ የዴሞክራሲ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ተቋማት ግንባታ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ይህም ማለት አንድ ሀገር የገነባችውን ተቋም ትመስላለች በሚል እሳቤ ነው፡፡

ይህንን ተከትሎም ሃገራችን ባለፉት ሁለት አስርት አመታት አስደናቂ የተባለለት ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማስመዝገቧን የተለያዩ አለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡት ቆይተዋል። አንዳንድ ጥናቶችም ይህንኑን አረጋግጠዋል፡፡

ከሂደት በኋላ ግን የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት በተለያዩ ምክንያቶች መፈተን የጀመረ ሲሆን፤ ሙስና እና ብልሹ አሰራር በዋነኝነት ይችግሩ መንስኤ ሆነው ይጠቀሳሉ።

ለአብነትም  የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መጨመር፣ በብሄራዊ ባንክ ተቀማጭ የውጪ ሀገር ገንዘብ እጥረት፣ የውጭ ንግድ በሚፈለገው ልክ አለማደግ፣ የአገር ውስጥ ቁጠባና ኢንቨስትመንት አለመመጣጠን፣  የውጭ ብድር ዕዳ መጨመር እና የድርቅ ተጽዕኖ መኖሩ ለኢኮኖሚው እድገት ማነቆ እንደሆኑ ይነገራል።

የሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት የግል ባለሃብቶችን ባሳተፈ መልኩ  ሰፊ  መሰረት ያልነበረው ከመንግስት የሚቀርብለት የድጋፍ እና  የብድር አቅርቦት ማነስ፣ የግሉን ዘርፍ ሊደግፍ የሚችል ግልፅ የሆነ ፖሊስ እና የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ፤ የሀገር ውስጥ ባለሃብት አቅም በሚፈለገው ልክ አለመጎልበት ለኢኮኖሚዊ ቀጣይነት ትልቅ ተግዳሮት ሆኖት ከመቆየቱ ባሻገርም አስተማማኝ የሆነ የስራ ዕድል ፈጠራ እንዳይኖር አድርጎታል። መንግስት የገበያ ጉድለትን እየሞላ በሂደት ለግል ባለሃብቶች እየለቀቀ ይሄዳል የሚል እሳቤ ቢኖርም ተግባራዊነቱ ግን ወደኋላ የቀረ ሆኗል። በአንፃሩ ደግሞ መንግስት በውጭ ብድር የጀመራቸው ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሳይበቁ የብድር መክፈያ ጊዜያቸው በመድረሱ አገሪቷ ወደከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ የገባችበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።       

አገሪቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዝብ ስትበደር ቆይታ አሁን መክፈያው ጊዜው ሲደርስ ለመክፈል ከፍተኛ ችግር ከመፈጠሩም ባለፈ በመንግስት የሚተዳደሩ ተቋማትና ፕሮጀክቶች አፈፃፀም እጅጉን የተዳከመ መሆኑ ሪፎርሙ እንዲተገበር አስገዳጅ ምክኒያት ሆኗል፡፡ ፈጣን የሆነ የማሻሻያ እርምጃ ካልተወሰደ ኢኮኖሚውን ወደ ኋላ የሚመለስና ሃገሪቷን ወደማትወጣው የድህነት አዝቅት ውስጥ ሊያስገባት  ይችላልበማለትም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ አስጠንቅቀው ነበር።

በዚህ ምክንያት አገራችን አዲስ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማድረግ መገደዷን መንግስት በቅርቡ ገልጾ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል።ከእርምጃዎቹ መካከል የወጪ ወይም የሃብት አጠቃቀምንና ብክነትን ለመከላከልም መንግስት በእጁ ባሉት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች ላይ ትኩረቱ በመስጠት ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት እንዲያስችለው በሙስና እና ብልሹ አስራረ የተጠረጠሩ የመንግስተ አመራሮችን በህግ ተጠያቂ በማድረግ እና የተቋማት አደረጃጀት እያዘመነ ይገኛል።     

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርበው እንደተናገሩት መንግስት በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ የልማት ድርጅቶችን በከፊልም ይሁን ሙሉ በሙሉ በመሸጥ በገንዘብ ምንጭነት ሂሳብ ስሌት ውስጥ በማስገባት የኢኮኖሚ ለውጥ ማድረግ ማስፈለጉን አስረድተዋል።እነዚህን ታላላቅ የልማት ድርጅቶች በሙሉ ሆነ በከፊል  ሽያጭ በሚያካሂድበት ወቅት ሃገሪቱ በምትከተለው የልማታዊ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ተገቢ በሆነ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት እንደሚከናወን በማንሳት።

ልማታዊ መንግስት እንደ ፖሊቲካ ኢኮኖሚ ርዕዮተ-ዓለም ሲታይ ወደ ካፒታሊስት ስርዓት የሚያሸጋግር ድልድይ እንጂ ራሱን ችሎ ሊቀጥል የሚችል ግብ እንዳልሆነ ይታወቃል።

የልማታዊ መንግስት መጨረሻ ግብ በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግስትን ሚና በማሳነስ በተቃራኒው የግል ባለሃብቱን ሚና አጎልብቶ የካፒታሊስት ወይም የሊበራል ኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ነው።

በሃገር ውስጥ የሚያከናውነውን ልማት እውን ለማድረግ፣ የግሉ ባለሃብት ልማታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስትም በተመረጡ የልማት አውታሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ልማቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ጥረት ማድረጉ ግን አይቀርም፡፡

ለቀጣይም ቢሆን ሃብት አንድ ቦታ በማይከማችበት ሁኔታ በልማት ሂደቱ ውስጥ የመንግስት አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የግሉ ባለሃብት ሚና ግን በየጊዜው እያደግ መሄድ ይኖርበታል።

ስለሆነም መንግስት ከገንዘብ እጥረት አኳያ ያቀዳቸውን የተለያዩ የልማት አውታሮች መፈፀም ያስችለው ዘንድ እንደ ቴሌ፣ አየር መንገድ፣ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የመሳሰሉ ግዙፍ  ተቋማትን በከፊል ለግሉ ባለሃብቱ ለማስተላለፍ በጥናት ላይ ይገኛል።

ይህ መሆኑ መንግስት ከ85 በመቶ በላይ የኢኮኖሚያችን ዋነኛ መሰረት የሆነው አርሶ አደር በሚገኝበት ገጠር ወስጥ ትምህርት፣ ጤናን፣ ግብርና፣ ንፁሁ ውሃን እንዲሁም የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ገንብቶ ለህብረተሰቡ የመስጠት አቅሙን ማጎልበት  እንደሚያስችለው ይታመናል፡፡በተጨማሪ የሃገራችን ባለሃብቶች አቅም እየጎለበተ ሲመጣ ለበርካታ ስራ አጥ ለሆኑ ወጣቶቻችን ሰፊ የሆነ የስራ እድል ይፈጥራል።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መንግስት በቀየሳቸው ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በማህበራዊ ዘርፎች መስክ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር በሀገሪቱ ምክር ቤት ቃለመሀላ ፈጽመው ስልጣን በያዙበት የሹመታቸው ዕለት ያደረጉት የብዙሃንን ቀልብ የሳበ ንግግር እና የገቧቸው ቃሎችም ከጅምሩ ብዙ ተስፋ እንዲጣልባቸው አድርጓል።

ብዙም ሳይቆዩ በሹመታቸው እለት የተናገሯቸውን እና ቃል የገቧቸውን ጉዳዮች ወደ ተግባር መቀየር ሲጀምሩ ደግሞ በህዝቡ ዘንድ የነበረው ተስፋ ወደ ሰፊ ድጋፍ እንዲቀየር አድርጓል።

በኢኮኖሚው መስክ መንግስት  ቁልፍ በሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም በቴሌኮም፣ በሃይል እና በአየር ትራንስፖርት በከፊልና በሙሉ ወደ ግል ማዞር በቀዳሚነት ከሚጠቀሱላቸው አበይት ውሳኔዎቻቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

የዚህ ተግባራዊ አፈፃፀም ውስብስብ እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጠንካራ ተቃውሞ ሊያጋጥመው የሚችል ቢሆንም፤ የጠቅላይ ሚኒሰተር አቢይ መንግስት የኢኮኖሚ ስርዓቱን ለማሻሻል ሰፊ ስራዎች እየሰራ ይገኛሉ፡፡

ከለውጡ በኋላም ኢኮኖሚው በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ያልታየው ከለውጥ በፊት የሃገሪቱ ኢኮኖሚው ችግር ውስጥ ሆኖ ስለቆየ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

በዚህም በርካታ ሀገራት ለውጡን በመደገፋቸው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት እያሳየ ይገኛል፡፡ በአሁኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ውስጥ የኢኮኖሚ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም እንደቁልፍ ለውጥ የሚወሰድ ነው።

ታላላቅ የመንግስት ኩባንያዎች በሙሉም ሆነ በከፊል ወደ  ግሉ ዘርፍ ለማዞር እንቅስቃሴ መጀመሩ ላለፉት 20 አመታት በመንግስት እጅ ተይዘው የቆዩ ትላልቅ የመንግስት ኩባንያዎችን ትልቁን ድርሻ ይዞ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች፣ ዲያስፓራዎችና በዘርፉ እውቀት ያላቸው የውጭ ኩባንያዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ መወሰኑ የተቋማቱን የምርት ጥራት በመጨመር የኢኮኖሚ እድገቱን እንደሚያፋጥን ተስፋ ተጥሎበታል።

ብቃት ያለው የሰው ሀይል በመያዝ፣ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ባለሃብቶች ከተሰማሩባቸው ድርጅቶቹን አለም አቀፍ ተወዳደሪ ማድረግ ያስችላቸዋልና።

ለግል ባለሀብቶች ቢተላለፉ የንግድ ውድድርን በመፍጠር ጥራት ያለው ምርት በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ለዜጎች የበለጠ ስራ እድል በመፍጠር  ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያደርጋል።

ኢትዮጵያ የኢንደስትሪ ፓርኮችን በመገንባት እና ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ  የማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩን የአመታዊ ጥቅል ምርት በማሳደግ የኤክስፖርት መጠኑ እንድሻሻል ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡

የሀዋሳ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ኮምቦልቻ፣ ጅማ፣  ድሬዳዋ፣  አዳማ፣ ደብረ ብርሃን፣  እና ቦሌ ለሚ የኢንደስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ወደ ስራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸው ለወደፊቱ ሃገሪቱ ለምታስመዘግበው ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዲያስፖራው ብድር ለማቅረብ መወሰኑ በሃገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ሲያስቀምጡ እስከ 50 ሺህ ዶላር ብቻ የነበረውን ገደብ ማንሳቱ እና ዲያስፖራው የተለያዩ የውጭ ሀራት ገንዘብ እንደ ዶላር፣ ዩሮና የመሳሰሉትን መቆጠብ መቻሉ በሃገር ወስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ  ጉልህ አስተዋፅዖ አለው።

ቤላ በኩል ዲያስፖራው 20% የውጪ ሀገር ገንዘብ ተቀማጭ ካደረገ ባንኮች የቤት መስሪያ ብደር ማቅረብ መቻላቸው የውጪ ምንዛሬን እጥረት ከማቃለል አንፃር የሚኖረው ሚና ቀላል አይሆንም።

መንግስት በመስኖ እርሻ ፕሮጀክቶች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ከፍተኛ የሆነ በጀት በመመደብ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የተነደፈውን የእድገት ትራንስፎርሜሽን  እቅድ ለማሳካት መንግስት የጀመራቸውን መለስተኛና ትልልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ከማስፋፋትና ከማጠናከር ባሻገር አዳዲሶችንም በመገንባት፣ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግና ግብዓትና ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በጥራት በማቅረብ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማዳበር ያስችለዋል፡፡

ይህ ሲሆን  ለመስኖ እርሻ ልማት ያለው የውኃ አቅም እና በዘርፉ ሊለማ የሚችለው መሬት ሙሉ በሙሉ መጠቀም በምያስችል መልኩ ባለሃብቶች መዋለ ነዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ በዘርፉ ሰፊ የሆነ የስራ እድል ይፈጥራሉ፡፡

በአጠቃለይ አሁን በምንገኝበት የኢኮኖሚ አቅም እና ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መንግስት ተገቢ ነው ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ ከዚህ በፊት ያጋጠሙትን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት እንዲያስችለው ትኩረት ተሰጥቶ የጀመራቸውን ጥረቶች  አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም