በሀዋሳ በሲዳማ ሴቶች የሚካሄደው ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ

65

ሀዋሳ መጋቢት 28/2011 ከሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ አስመልከቶ በመጪው  ማክሰኞ በሴቶች የተጠራው ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው ፖሊስ፣ ከሲዳማ ዞን ፖሊስና ከሰልፉ አስተባባሪዎች ጋር በመሆን በሰልፉና በዝግጀቱ ዙሪያ ትላንት መግለጫ ሰጥቷል ።

የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ እንደገለፁት በመጪው  ማክሰኞ በሲዳማ ሴቶች አማካኝነት በሀዋሳ ከተማ ለሚካሄደው ሰልፍ ፍቃድ መሰጠቱን አረጋግጠዋል።

ሰልፉ በሴቶች ብቻ የሚካሄድ መሆኑን አመልክተው ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከከተማው፣ ከክልል፣ ከዞንና ከፌደራል በተውጣጣ ኃይል ጸጥታ የማስከበር ስራ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

ሰልፉ የህዝቡ መደበኛ እንቅስቃሴ ሳይቋርጥ እንደሚካሄድ አማላክተው በዕለት የተወሰኑ የሀዋሳ ከተማ መንገዶች ብቻ ከንጋቱ 12:00 ሰዓት እስከ ቀኑ 7:00 ሰዓት ዝግ እንደሚሆኑ  አመላክተዋል ።

የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወጣት ሰላማዊት ሾና "የሰልፉ ዓላማ የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ምላሽ መዘግየቱን በመግለፅ ምላሹ እንዲፋጠን ድምፅ ማሰማት ነው" ብላለች ።

እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ በሰልፉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ብቻ ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም