ኢትዮጵያ 7ኛውን የአፍሪካ ዓይነ ስውራን ፎረም እንድታዘጋጅ ተመረጠች

89

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011 ኢትዮጵያ 7ኛውን የአፍሪካ ዓይነ-ስውራን ፎረም እንድታዘጋጅ ተመረጠች።

ፎረሙ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ የዓይነ ስውራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ወሰን አለሙ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ከሚገኙና 59 ዓመታትን ካስቆጠሩ የዓይነ ስውራን ማህበራት የኢትዮጵያው ቀዳሚና አዲስ አበባም ለዚህ ምቹ በመሆኗ ፎረሙን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫዋ አዲስ አበባ የዓይነ-ስውራን ፎረምን ለማዘጋጀት ምቹ መሆኗን ያወሱት የማህበሩ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሤ የዓይነ ስውራንን መብት ለማስጠበቅ ብዙ ለጀመረች ግን ጉዞዋን ላልጨረሰች አገር ጠቀሜታው ብዙ እንደሆነ ገልፀዋል።

ፎረሙ የዓይነ ስውራንን ፍላጎት ለመመለስ ገንዘባቸውን በቼክ በማያዘዋውሩባት፣ ብሬል መጠየቅ እንደ መብት በማይታይባትና ታሳቢ የማይደረግ መሠረተ ልማት በሚሰራባት አገር መዘጋጀቱም መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

አገሪቱ ለዘርፉ ትኩረት እንድትሰጥ ያደርጋታል ነው ያሉት።

ፎረሙ እ.አ.አ 1996 ዓ.ም ከተመሠረተ በኋላ በኡጋንዳ፣ በጋናና በኬንያ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የአፍሪካ አይነ-ስውርነት ፎረም ከመስከረም 26-30 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል።

“ህይወትን በተደራሽነት በፈጠራና ትምህርት ማሸጋገር” በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው ፎረም ዘርፉን የሚያሻሽሉ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች፣ የተሻሉ የፈጠራ ስራዎች፣ የጥናት ውጤቶች እንዲሁም በአገራት መካከል የልምድ ልውውጥ ይደረጋል።

በፎረሙ ላይ ዘርፉን ማገዝ የሚሹ ግለሰቦችና ተቋማት መገኘት የሚችሉ ሲሆን ወጪው በማህበሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓይነ ስውርነት ላይ በሚሰራው ፐርኪንስ እንደሚሸፈን ተገልጿል።

500 የሚደርሱ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙበትም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር በ59 ዓመታት ጉዞው በአምስት ክልሎች 31 ቅርንጫፎችን በመክፈት መንግስት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል እያደረገም ይገኛል።

ከ13 ዓመት በፊት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ በኢትዮጵያ ሶስት ሚሊዮን ዓይነ ስውራን እንደሚገኙ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም