በጋምቤላ ክልል ወንጀሎችን ለመከላከል ህግ አስከባሪዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ

409

ጋምቤላ መጋቢት 27/2011 በጋምቤላ ክልል የሚታየውን ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል ህግ አስከባሪዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በክልሉ ህግ በማስከበር ላይ የተሰማሩ የፀጥታ አካላት በአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በሚቻልበት ዙሪያ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጋር በጋምቤላ ከተማ  ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ  ወቅት እንደተገለጸው በአካባቢው በተለይም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ፣ ሌብነትና ሌሎችም ህገ ወጥ ተግባራት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ህግን በማስከበር ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙያዊ ግዴታቸውን በአግባቡ አለመወታጣቸው መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል ኮማንደር ሳይመን ዴንግ እንዳሉት አንዳንድ የክልሉ ፖሊስ አባላት የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ግዴታ ወደ ጎን በመተው ለራሳቸው ጥቅም የሚሯሯጡበት ሁኔታ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማናቸውም የፖሊስ አባላት ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ወደ ሙያቸው ሲገቡ ቃል በገቡት መሰረት የህብረተሰቡን ጥቅም ማስቀደም እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ዋና ኢንስፔክተር ዋንጫ ኡጉድ በበኩላቸው በፖሊስ አባላት በኩል የሚታየው የመረጃ አያያዝ ክፍተት በክልሉ ለሚስተዋለው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም  የፖሊስ አባላቱ ከህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ጋር በጥቅም መተሳሰራቸው ሌላው ችግር  እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት በኮሚሽኑ በተለይም ከደረጃ እድገትና ከማዕረግ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሙያንና አቅምን ያላገናዘቡ ምደባዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ  ምክትል ኮማንደር አገዋ ኡጁሉ ናቸው፡፡

በክልሉ አስተማማኝ የፀጥታ ሥርዓትን ለመዘርጋት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የሌብነትና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል የሰው ኃይል ምደባን አቅሙን ያገናዘበ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኢንስፔክተር ኡቻቲ ኡጁሉ  በሰጡት አስተያየት “በክልሉ የጸጥታ አካላት ዘንድ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በተለይም ከአደረጃጀት ጋር ተያይዘው ያሉት ጉዳዮች ሊፈተሹ ይገባል ” ብለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በውይይት መድረኩ እንዳሉት  በፀጥታ አካላት ዘንድ የሚታዩ የስነ ምግባርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ያለባቸው አባላትን የህዝቡን ሰላም ሊያስጠብቁ አይችሉም፡፡

እነዚህን አካላት በመለየትና መልሶ በማደራጀት የህዝብ አገልጋይ ተቋም እንዲሆን በማድረግ ረገድ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በተለይም በወንጀል ምርመራ አካባቢ የሚታዩ ክፍተቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲስተካከሉ ኮሚሽኑ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር ኡማን ኡጋላ  በኮሚሽኑ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል ኮሚቴ በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡