የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ረቂቅ አዋጅ ድጋፍና ተቃውሞ ገጥሞታል

64

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011  ዜጎችን ለሁከትና ለእርስ በእርስ ግጭት የሚዳርጉ መረጃዎችን ለመከላከል የወጣው የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ረቂቅ አዋጅ ድጋፍም ተቃውሞም ገጥሞታል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በተለያዩ መንገዶች የሚለቀቁ ግጭት፣ ሁከትና መፈናቀልን የሚያባብሱ ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል።

በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውይይት ተካሂዶል ።

የረቂቅ አዋጁን መነሻ ያቀረቡት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ምክትል ዓቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እንዳሉት ራሱን የቻለ የጥላቻ ንግግር መቆጣጠር የሚያስችል ህግ አልነበረም።

በጥላቻ ንግግርና በሃሰተኛ መረጃዎች አማካኝነት ዜጎች ለሁከት፣ ብጥብጥና ግጭት ይዳረጋሉ፣ ከቀዬአቸውም ይፈናቀላሉ ይህ ደግሞ መቆም አለበት ብለዋል።

በመሆኑም የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ፣ ያለውን የዜጎች መፈናቀልና ስጋት ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሰረተ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት መቆጣጠሪያ ረቂቅ ሰነድ 'ለማዘጋጀት ተገደናል ነው' ያሉት።

በረቂቅ አዋጁ መሰረት ንግግር ማለት በቃል፣ በጽሁፍ፣ በምስልና በሥዕል፣ በቅርፃ ቅርፅና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች መልዕክት የማስተላለፍ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።

"ሆነ ብሎ የሌላን ግለሰብ፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማኅበረተሰብ፣ ብሄርን፣ ኃይማኖት፣ ቀለም፣ ፆታን፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ ዜግነትን ስደተኝነትን፣ ቋንቋን፣ ውጫዊ ገፅታን መሰረት በማድረግ እኩይ አድርጎ የሚስል፣ የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ መድልዎ እንዲፈጸም ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ የጥላቻ ንግግር" ተብሎ ተተርጉሟል።

ይሁን እንጂ በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የቀረበው የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ረቂቅ አዋጅ በተወያዮቹ ዘንድ ድጋፍና ተቃውሞን አስተናግዷል።

የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ሊቀ መንበር አቶ ትግስቱ አወሉ የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃዎችን በመቅጣት ከመቆጣጠር ሥነ ምግባርን በማስተማርና በብሮድካስት ህግ ማስተካከል ይቻላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ለማጎልበት ዜጎችን ማስተማርና በቂና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ እንጂ በህግ መቅጣት ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል።

የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የመቅጫ ህግ ከማውጣት ሥነ ምግባር ማስተማሪያ መንገዶች ቢቀረጹ መልካም እንደሆነ በመጠቆም።

የመላው ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዚዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራው በበኩላቸው ህጉ መውጣቱ ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ነው የገለጹት።

የጥላቻ ንግግር የሚያቀራርብ ሳይሆን የሚያራርቅ በመሆኑ በማያሻማና የዜጎችን በነጻነት የመናገር መብት በማይገድብ መልኩ በጥንቃቄ ተመርምሮ መውጣት አለበት ብለዋል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የጥላቻ ንግግር ትርጉም በሚብራራበት አገባብ "ሆነ ብሎ" የሚለው ሃረግ አሻሚና ለትርጉም የተጋለጠ በመሆኑ በሚገባ መብራራት እንዳለበት ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት በጥንቃቄ ሊታዩ የሚገባቸው በርካታ ማስተካከያዎች ሊደረጉ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

"ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ሀሰተኛ መረጃ ሆነ ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ ማድረስ የተከተከለ ነው" የሚለውን አንቀፅ ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተቀባይነት ያለው ትችት፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ክርክር፣ ለትምህርታዊና ለምርምር የሚደረጉ ንግግሮች እንደ ጥላቻ ንግግር አይቆጠሩም ተብሏል።

"በቅን ልቦና የተደረጉ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች" በሚለው አንቀፅ ስር "ቅን ልቦና" የሚለው ሃረግ ለትርጉም የተጋለጠ በመሆኑ ረቂቁ በጥንቃቄ ሊፈተሽ ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም