ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በሥራ ዓለም ውጤታማ እንዲሆኑ ለማገዝ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

84

ሀዋሳ መጋቢት 27/2011 ተመራቂ ተማሪዎች በሥራ ዓለም የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በብቃት ማለፍ እንዲችሉና በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማገዝ እየሰራ መሆኑን የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ) ጋር በመተባበር ለተመረጡ የ2011 ተመራቂ ተመሪዎች የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የውጤታማነት አሠራር ሥርዐት ዩኒት ኃላፊዶክተር ታዬ ገብረማርያም እንደገለጹት ተማሪዎች ከተቋሙ ብቁ ሆነው እንዲወጡና በሥራ ዓለም ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው፡፡

"ስልጠናው የእዚሁ ግብ አንድ አካል ነው" ያሉት ኃላፊው፣ ተመራቂዎች ሥራ ለመቀጠር በሚወዳደሩበት ወቅት ብቁ ሆነው እንዲቀርቡና ተግዳሮቶችን በብቃት ለማለፍ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የራሳቸውን የሥራ እድል ፈጥረው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዩኒት ኃላፊው ገለጻ ስልጠናው ቀጣይነት ያለው ሲሆን እስከ ትምህርት ዘመኑ ማብቂያ ድረስም አብዛኛውን የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎችን ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረትም ዩኒቨርሲቲው ከግልና ከመንግስት ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት የከፍተኛ ትምህርት ኦፊሰር አቶ ሠላሙ ቃሎሬ በበኩላቸው ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ የተሻለ ሥራ እንዲያገኙና የራሳቸውን ሥራ መፍጠር እንዲችሉ የሚያገዝ የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር በተደረገ የዳሰሳ ጥናት አምና ከዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ ስምንት ሺህ 400 ተማሪዎች መካከል እስካሁን ከ60 በመቶ በላይ የሚጠጉት ሥራ እንዳላገኙ ተረጋግጧል፡፡

ከሙያዊ እውቀት ይልቅ የእርስ በእርስ ግንኙነት፣ የሥነ ምግባርና ሌሎች የማህበራዊ ክህሎት ክፍተቶች ለዚህ ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን አመልክተዋል ፡፡

ስለጠናው በሙከራ ደረጃ መሰጠቱን ገልፀው ውጤታማነቱ እየተፈተሸ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የማስፋት ሥር እንደሚከናወን አስረድተዋል ፡፡

ከዚህ በፊት በሠለጠንኩበት ሙያ ተቀጥሬ ለመስራት ብቻ ነበር የማስበው ያለችው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው  የኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ምህንድስና የአምስተኛ ዓመት ተማሪ ጥሩቃል አለሙ ናት፡፡

በዝንባሌዋ በግል ሥራ ተሰማርታ እንዴት ውጤታማ መሆን እንደምትችል ከስልጠናነው በቂ እውቀት ማግኘቷን ተናግራለች ፡፡

"የምፈልገውን ሥራ እስካገኝ ድረስ ቁጭ ብዬ ሥራ መጠበቅእንደሌለብኝ ግንዛቤ አግኝቺያለሁ" ብላለች ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የውሃ ሀብት ምህንድስና አምስተኛ ዓመት ተማሪ ኤፍሬም ይመር በበኩሉ በስራው ዓለም ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆንና የራሱን የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ከህሎት በስልጠናው ማግኘቱን ተናግሯል ፡፡

በስራ ፈጠራ፣ በእርስ በርስ ግንኙነትና በማህበራዊ ክህሎት ላይ አተኩሮ ለሦስት ቀናት በተሰጠው ሥልጠና 250 የሚሆኑ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች መካፈላቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም