ግዙፍ የጀርመን ኩባንያ ሲመንስ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

95

አዲስ አበባ  መጋቢት 27/2011 ሲመንስ የተሰኘው የጀርመን ኢንዱስቲሪያል ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአየር ትራንስፖርት ኢንደስትሪ ልማት ዘርፍ ተባብረው ለመስራት ተስማሙ።

አየር መንገዱና ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ በአፍሪካ በዓይነቱ ትልቅ ነው የተባለ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ማሰልጠኛ ተቋም የመገንባት እቅድ እንዳላቸውም ተመልከቷል።

ኮምፒውተርን ጨምሮ በተለያዩ ኢንዱስቲሪያል የኤሌክተሮኒክስና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ ሥራ የሚታወቀው  ዓለም አቀፍ ኩባንያ  ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ጆ ካሴር ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን አካዳሚን ጎብኝተዋል። 

በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው ኩባንያውና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቴክኖሎጂ አቅምና ልምድ በማጎልበት በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ለማስቀጠል ተስማምተዋል።

ኩባንያቸው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ዋነኛ አጋር ሆኖ የመስራት ፍላጎት እንዳለው የሲመንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አረጋግጠዋል።

አዲስ የምሰለ በረራ ሶፍትዌር ለኢትዮጵያ አቬይሽን ኢንዱስትሪ ለማሰተዋወቅም ኩባንያው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ወልደማሪያም በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ በሚጠቀማቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ኩባንያው ጥሩ አቅም እንደሚሆነው ተናግረዋል።

ኩባንያው ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ውጪ ልከን ብዙ ወጪ ማውጣትና ጊዜ ማጥፋት ሳያስፈልግ በአገር ውስጥ ማሰልጠን እንደሚቻልም ነው የተናገሩት። 

አየር መንገዱ አድማሱን በማስፋት ለአውሮፕላን ጥገና የሚውሉ መሳሪያዎችን አገር ውስጥ ለማምረት፣ በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ኤርፖርቶችን ለመገንባት፣ ለመጠገንና ለማደራጀት ባለው እቅድ ላይ ከኩባንያው ጋር በጋራ እንደሚሰራም አክለዋል።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደበበ፤ ከኩባንያው ጋር በጋራ በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በአፍሪካ በአይነቱና በይዘቱ ትልቅ የማሰልጠኛ ተቋም ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።

ሲመንስ የጀርመን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሲሆን ኩባንያው በቀጣይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተጠቁሟል።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን በትናንትናው እለትም በኢትዮጵያ የፋብሪካዎችን የማምረት ዑደት ቀመር /የሲማቲክ አውቶሜሽን/ ማዕከል ለመክፈት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርመዋል። 

የጀርመን የቴክኖሎጂ ተቋማት በኢትዮጵያ ማዕከል መክፈቱ የቴክሎጂና እውቀት ሽግግር ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።

ማዕከሉ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ ተመርቀው የሚወጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎችን በቴክኖሎጂ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም