የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ችግሮች የጥጥ ልማት ተወዳዳሪ እንዳይሆን እያደረጉት ነው

71

አዲስ አበባ  መጋቢት 27/2011 በኢትዮጵያ የጥጥ ልማት ላይ የሚታዩ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ችግሮች ዘርፉ ተወዳዳሪ እንዳይሆን ማነቆ ሆነዋል ተባለ።

የኢትዮጵያ ጥጥ አምራቾችና መዳመጫ ባለንብረቶች ማህበር ለሁለት ቀናት የሚያካሂደውን ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ ጀምሯል።     

ጉባዔው የጥጥ ምርት ዓለም አቀፍ ደረጃ ምን እንደሚመስል፣ ምን ያህል ገቢና ምርት እየተገኘ እንደሆነ፣ የአገራት ተሞክርና በኢትዮጵያ የደረሰበት ደረጃ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።     

የማህበሩ ጄኔራል ማናጀር አቶ አሰፋ አጋ በጥጥ ልማት ተሞክሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ህንድ፣ ቻይና፣ ብራዚልና አሜሪካ ከፍተኛ ምርት እንደሚያመርቱ ገለጻ አድርገዋል። 

ህንድ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ ቻይና 5 ነጥብ 7፣ አሜሪካ 4 ነጥብ 5 እና ብራዚል ከ2 ሚሊዮን ቶን በላይ ጥጥ በዓመት ያመርታሉ።    

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጥጥ አምራች የአፍሪካ አገራት ከሌላው ዓለም ጋር ሲነጻጸር የሚጠበቀውን ያህል ምርት እየተገኘ አለመሆኑንና ምክንያቱ ደግሞ እሴት አለመጨሩ እንደሆነ ተናግረዋል።  

በጉባዔው ላይ ለጥጥ ልማት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረትና ስርጭት ችግሮች ዘርፉን እየተገዳደሩት መሆኑም ተነስቷል። 

ተፈላጊ ምርታማ ዝርያዎች አለመኖር፣ የተባይ ማጥፊያ ኬሚካልና የፋይናስ አቅርቦት እጥረት ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውም ተገልጿል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሼህ ሶፉ ዑመር የጥጥ ምርት ለመሰብሰብ የሰው ኃይል እጥረት እየጋጠመ በመሆኑ መልቀሚያ ማሽን ሊኖር ይገባል ብለዋል።   

ለእርሻ መሳሪያ ግብዓት እንዲሟላ ጥያቄ ሲቀርብ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ለመጠበቅ እንገደዳለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ የጥጥ መዳመጫ ችግርን ለማቃለል በልማት ባንክ በኩል ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሰራል ቢባልም 'ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም' ነው ያሉት።      

"አሁን እየተቸገርን ያለነው መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ይገባል ነገር ግን ሲፈጽም አይታይም፤ መንግሥት ሊያስብበት ይገባል'' ሲሉም አክለዋል።   

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በበኩሉ በጥጥ ልማት ዘርፍ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የ15 ዓመት ስትራቴጂ ተንድፎ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻል። 

በኢንስቲትዩቱ የጥጥ ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አሰፋ በመስኩ ልማት የሚያጋጥሙ ችግሮች ተለይተው በስትራቴጂው መሰረት መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራ ነው ብለዋል።     

ከምርት ሽፋን አኳያም በአገሪቷ ለእርሻ ከሚውለው መሬት አንድ ሚሊዮን ሄክታሩን ለጥጥ ልማት ለማዋል መታቀዱን ጠቁመዋል።

ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተለይም ዘር አባዝተው የሚያቀርቡ ስድስት ተቋማት ተመርጠው እያቀረቡ መሆኑን ገልጸው በዓመት በአማካይ እስከ 8 ሺህ የተሻሻለ ዘር እየቀረበ ነው።

ይህም ለምርትና ምርታማነት ማደግ የጎላ ሚና እየጨወተ ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ በተያዘው ዓመት እስከ 180 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ልማት ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን የዘር፣ የኬሚካል አቅርቦትና ለአልሚዎችም የቴክኒክ ድጋፍ ይደረጋል።

ከግብርና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች ጋር በመተባበርም ለአምራቾች ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም