ለበልግ እርሻቸው ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ማግኘት እንዳልቻሉ አርሶ አደሮች ገለጹ

214

 አዳማ/ደብረ ማርቆስ መጋቢት 27 / 2011 ለበልግ አዝመራ የማሳ ዝግጅት ሥራቸውን ቢያጠናቅቁም ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ማግኘት እንዳልቻሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአርሲ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው የአፈር ማዳበሪያ የመጠቀም ፍላጎታቸው ቢያድግም የዋጋ ጭማሪ ከአቅም በላይ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

በአርሲ ዞን በሌ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር በቀለ ያዳቴ እንደገለጹት የእርሻ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ለዘር ዝግጁ አድርገዋል።

እስካሁን ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ጨምሮ ምንም አይነት የግብርና ግብዓት እንዳላገኙ ገልጸው በአሁኑ ወቅት በአካባቢው መጣል የጀመረው ዝናብ ሳይቆም የምርት ማሳደጊያ ግብአት ፈጥኖ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል። 

ከሰባት ሄክታር በላይ የእርሻ ማሳ ማዘጋጀታቸውን የገለጹት አርሶ አደር በቀለ ለዚህም ከ10 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና አራት ኩንታል ማዳባሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

በአርሲ ዞን ሱዴ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ሁሴን ሃጂ አህመድ በበኩላቸው ለበልግ እርሻው 10 ሄክታር መሬት አርሰው ቢያዘጋጁም በግብዓት እጦት ምክንያት ዝናቡን ተከትለው ዘር መዝራት እንዳልቻሉ ነው የገለጹት።

" በአሁኑ ወቅት ትልቁ ማነቆ እየሆነብን ያለው  የአፈር ማዳባሪያን ጨምሮ የስንዴ፣ የገብስ፣ የቦቆሎና የጥራጥሬ ምርጥ ዘር በወቅቱ አለመቅረብ ነው " ብለዋል።

" የምርት ማሳደጊያ ግብዓት እስካሁን ባለመድረሱ የመዝሪያ ወቅት እንዳያልፍብን ሰግቺያለሁ " ብለዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት በዘንድሮ ዓመት ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ በመስመር አዘራር፣ በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ አጠቃቀም እንዲሁም በሰብል እንክብካቤ ላይ የክህሎትና የአቅም ግንባታ ስልጠና አግኝተዋል።

አምና ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሮቹ መንግስት ፈጥኖ በመድረስ ችግሮቻቸውን እንዲፈታና ዘንድሮም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የአርሲ ዞን የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባቡ ዋቆ በባኩላቸው በዞኑ ከሚገኙ 25 ወረዳዎች በ12ቱ ላይ የበልግ እርሻ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በዞኑ አጠቃላይ ከሚታረሰው የእርሻ መሬት 49 በመቶ የሚሸፈነው በበልግ አዝመራ በመሆኑ ለሰብሉ ልማት በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የበልግ አዝመራውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ አርሶ አደሩ የእርሻ ትራክተር በመንግስት ድጋፍና በኪራይ እንዲያገኝ በመደረጉ 134 ሺህ ሄክታር መሬት የማሳ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ ሙሉ የግብርና ፓኬጅ በአግባቡ እንዲጠቀም በማሳ ዝግጅት፣ በመስመር መዝራት፣ በምርጥ ዘርና በማዳበሪያ አጠቃቀም እንዲሁም በሰብል እንክብካቤ ላይ የክህሎትና የአቅም ግንባታ ስልጠና ለአርሶ አደሩና ለልማት ጣቢያ ሠራተኞች መስጠቱንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከ200ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብ በዩኒየኖችና መሰረታዊ ማህበራት አማካኝነት በየወረዳዎቹ ወደሚገኙ የማከማቻ መጋዘኖች መድረሱን የጠቀሱት ኃላፊው ሰሞኑን ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ከ15 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ፣ ገብስ፣ ቦቆሎና የጥራ ጥሬ ምርጥ ዘር በየወረዳዎች መድረሱን ጠቅሰው በዚህም 120 ሺህ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ በየነ ማሞ በበኩላቸው በክልሉ 726 ሺህ ሄክታር መሬት ለበልግ አዝመራ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እስካሁን ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና አንድ ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የአፈር መዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መቅረቡንም ተናግረዋል።

"በክልሉ ከበልግ አዝመራ ከ13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ሲሉም " ገልጸዋል።

በሌላ ዜና በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ የመጠቀም ፍላጎታቸው ቢያድግም የዋጋ ጭማሪ ገዝቶ ለመጠቀም ችግር ፈጥሮብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአዋበል ወረዳ የደጎራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገናነው አዲሴ ለኢዜአ እንዳሉት የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

" መሬቱ ማዳበሪያውን ለምዶታል፤ ያለማዳበሪያ መዝራት መክሰር ነው " ያሉት አርሶ አደሩ የመጠቀም ፍላጎታቸው ቢጨምርም በየጊዜው እያደገ የመጣው የዋጋ ጭማሬ ገዝተው ለመጠቀም ከአቅም በላይ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት 1 ሺህ 200 ብር የነበረው አንድ ኩንታል ዩ.ኤን.ቢ.ኤስ የአፈር ማዳበሪያ በዚህ ዓመት ብቻ 200 መቶ ብር መጨመሩን ገልፀዋል፡፡

"የዋጋ ጭማሪው ከሚያስፈልገኝ 6 ኩንታል ማዳበሪያ ሁለት ኩንታሉን ቀንሼ ለመግዛት አስገድዶኛል" ብለዋል።

በዞኑ የስናን ወረዳ ወለቄ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አንድነት ዳኘ በበኩላቸው የምርት መጠንን ለማሳደግ በቂ ማዳበሪያ ሲጠቀሙ ቢቆዩም በዚህ ዓመት በዋጋ ጭማሬ ምክንያት ከሚያስፈልጋቸው 10 ኩንታል ማዳበሪያ 5 ኩንታል ብቻ መግዛታቸውን አስረድተዋል።

ዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩ አምስት በጎቻቸውን ለመሸጥ እንዳስገደዳቸውና በዚህም የሚፈልጉትን ያህል ማዳበሪያ መግዛት እንዳልቻሉ የገለጹት ደግሞ በጎዛምን ወረዳ የሊባኖስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መኩሪያ ይበልጣል ናቸው።

ማዳበሪያ ለምርት እድገት መጨመር ካለው የጎላ ጠቀሜታ አንጻር መንግስት ለዋጋው ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን በበኩላቸው ከውጭ በሚመጣው የአፈር ማዳበሪያ ላይ የታየው ጭማሬ አገራዊ እንጂ በዞኑ ብቻ የተከሰተ አለመሆኑን ነው የገለጹት።

በተለይም በዚህ ዓመት ከውጭ ምንዛሬ እጥረትና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የዋጋ ልዩነት መኖሩን አምነዋል።

አርሶ አደሩ በሰው ሰራሽ ማዳበሪያ የዋጋ ጭማሬ ከመማረር በጉልበቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ሊጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም