የኦዴፓ ምስረታ በዓል በአምቦ ከተማ በድጋፍ ሰልፍ ተከበረ

79

አምቦ መጋቢት 27/2011 የምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ/ኦዴፓ/ የተመሰረተበት 29ኛው ዓመት በዓል ዛሬ በአምቦ ከተማ ደማቅ  የድጋፍ ሰልፍ ተከበረ፡፡ 

ነዋሪዎቹ  በድጋፍ ሰልፉ ወቅት እንዳሉት ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው፡፡

በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆንና በአንድ ዓመት ጊዜ ወስጥ የተገኘውን ውጤት ከዳር እንዲደርስ " የሰላም አምባሳደር"  በመሆን እንደሚደግፉ በሰጡት አስተያየትና ባሰሙት መፈክር አረጋግጠዋል፡፡

ከሰልፉ ተሳታፊዎች  መካከል የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አራርሴ ደበላ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸውና በሀገሪቱ ዘላቂነት ያለው አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ልማት እንዲጠናከር ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

" ሰላማችንን ለመጠበቅ ልጆቻችንንና ቤተሰቦቻችንን በመምከር ያገኘነውን ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይመለስ መንከባከብ  አለብን" ብለዋል፡፡

የተጀመረው ሰላምና ልማት ዘላቂ እንዲሆን ከመንግስት ጎን ሆነው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ከቶኬ ኩታዬ  ወረዳ  የመጡት  የድርጅቱ አባል  ወይዘሮ ቢሊሴ ጋሮማ ናቸው፡፡

አባገዳ  ለታ ዲርርሳ በበኩላቸው ህብረተሰቡ  ለሀሰተኛ  ወሬ ጆሮ ሳይሰጥ አንድነቱን ጠብቆ ለዘላቂ ሰላምና ልማት  ጠንክሮ መስራት እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአምቦ ከተማ ነዋሪው  ወጣት ናኦል ፈለቀ  በሀገሪቱ በመጣ ለውጥ ከአስር ዓመታት በላይ በስደት የተለዩት አባቱን በአካል በማግኘቱ እለቱን እንደ ራሱ ልደት እንዳከበረው ተናግራል፡፡

ለለውጡ ቀጣይነትና ውጤታማነት ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን የኦዴፓ ሊቀመንበር አቶ ገዛሀኝ ከበደ ለበዓሉ ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር  "ባለፈው ዓመት የተጀመረውን ለውጥ  ሁሉም ዜጋ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ሊጠብቀው ይገባል" ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም ወጣቱ ዋጋ ከፍሎ ያመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚራራጡትን ኃይሎች በንቃት በመከታተል ለህግ ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል፡፡

በዕለቱ በክብር እንግዳነት የተገኙት የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል  አቶ ካሳሁን ጎንፌ በበኩላቸው  በፖለቲካው የተገኘውን ድል በምጣኔ ሀብት ዘርፍም በመድገም ሀገራዊ ለውጡን ለማሳካት ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አቶ ካሳሁን እንዳሉት ኦዴፓ ለህዝቡ የገባውን ቃል እንደቅደም ተከተሉ ለመመለስ ጠንክሮ ይሰራል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትየዮጵያዊያን ጋር እንደ ከዚህ ቀደሙ በመተሳሰብ  አብሮ  እንዲኖር  የማይፈልጉ ኃይሎችን  ማሳፈር እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

በፈረስ ጉግስና  በድጋፍ ሰልፍ ታጅቦ በተከበረው የበዓሉ ስነስርዓት ከዞኑ የተውጣጡ የኦዴፓ አባላትና ደጋፊዎች ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ተማሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች  ፣አባገዳዎችና ሌሎችም ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኦዴፓ ምስረታ በዓል  መጋቢት 22/2011ዓ.ም. በዞን ደረጃ  በፓናል ውይይት መከበሩ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም