የፕሪሚየር ሊጉ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ

72

አዲስ አበባ  መጋቢት 27/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ።

ዛሬ በሀዋሳ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ነገ በሀዋሳ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማ ከባህርዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል።

እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት መከላከያ ከደደቢት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በክልል ከተሞች በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሊጉ መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከወላይታ ድቻ፣ በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር፣ በሀዋሳ ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ስሑል ሽረ በሜዳው ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ደደቢትን በዩጋንዳዊው ክሪዚስቶም ንታምቢ፣ በአህመድ ረሺድና በአቡከበር ናስር ግቦች 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። አቡከበር ናስር ግቧን ያስቆጠረው በፍጹም ቅጣት ምት ነው።

ለደደቢት ብቸኛውን ጎል እንዳለ ከበደ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን ወደ 28 ከፍ በማድረግ ከነበረበት 10ኛ ደረጃ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር መካሄድ የነበረበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ቡና ለብሔራዊ ቡድን ከሶስት በላይ ተጫዋች በማስመረጡ ምክንያት ጨዋታው የሚካሄድበት ቀን ተቀይሮ ትናንት መርሃ ግብሩ ተከናውኗል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ39 ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከተማ በ32፣ ሲዳማ ቡና በ31 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት በቅደም ተከተል ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በተመሳሳይ 11 ግቦች ሲመሩ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ10 ግቦች ይከተላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም