የጤና ዘርፍ ተባባሪ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

274

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2011 የጤና ዘርፍ ተግዳሮቶችን ለማቃለል ተባባሪ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን እንዲያጠናክሩ የጤና ሚኒስቴር ጠየቀ።

ሚኒስቴሩ ከነገ በስቲያ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የዓለም የጤና ቀን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶክተር ሊያ ታደሰ አገሪቱ በጤናው ዘርፍ የላቀ ውጤት እያስመዘገበች ቢሆንም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ተያያዥ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መቀዛቀዝ፣ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ ግብዓቶች አለማሟላት፣ የጤና ተቋማት ደረጃና የአገልግሎት ጥራት ፍተሻን በወጥነት አለመከወን ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ጠቅሰዋል።

የአካባቢ ንጽህና መጓደልና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትም ለተላላፊ በሽታዎች መከሰት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ነው ያሉት።

እነዚህንና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለማቃለል ከሚኒስቴሩ ጋር የሚሰሩ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን በማጎልበት የህብረተሰቡ ጤና እንዲጠበቅና በጤና ተቋማት ማግኘት ያለበትን አገልግሎት እንዲያገኝ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የዘንድሮው የዓለም የጤና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ትኩረት ለሚሹ ጉዳዮች መፍትሄ ማበጀትን መሰረት አድርጎ እንደሚከበርም ተናግረዋል።

ዕለቱ ሲከበር የጤናውን ዘርፍ ማነቆዎች በመፍታት ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት በዘላቂነት ተደራሽ ለማድረግ ቁርጠኝነትን በማጎልበት ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የህክምና ባለሙያዎች ስነ-ምግባር፣ የህክምና ስህተት፣ የተሟላና ጥራት ያለው አገልግሎት ማጎልበት፣ በጤና ጉዳዮች የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር በጤና ተቋማት በዘላቂነት እንዲሰራ ሚኒስቴሩ አሰራሩን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የዓለም የጤና ቀን ”ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን እናጠናክር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚከበረው።