ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ፍትሃዊ የሰብአዊ እርዳታ እየቀረበ ነው -የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን

176

አዲስ አበባ  መጋቢት 27/2011በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በሁሉም አካባቢ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየቀረበ ነው ሲል የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በመላው አገሪቱ ከሶስት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች በግጭት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

አብዛኞቹም ከደቡብ፣ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል የተፈናቀሉ መሆናቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። 

በኦሮሚያ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን፣ በደቡብ 840 ሺህ፣ በሶማሌ 700 ሺህ፣ በአማራ 102 ሺህ፣  በትግራይ 74 ሺህ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 61 ሺህ ተፈናቃዮች ይገኛሉ።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር  አቶ ደመና ዳሮቴ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ክልሎች በየአካባቢያቸው ለሚገኙት ተፈናቃዮች የሚያቀረቡት ድጋፍ ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለኮሚሽኑ ያሳውቃሉ።

ኮሚሽኑም ክልሎቹ በሚሰጡት የተረጂ ቁጥር መረጃ መሰረት  በ72 ሰዓት ውስጥ ለሰብአዊ እርዳታው ምላሽ መስጠት ይጀምራል።

በአሁኑ ወቅት እየቀረበ ካለው አጠቃላይ የሰብአዊ እርዳታ ውስጥ 60 በመቶው የሚሸፈነው መንግስት ሲሆን 22 በመቶው ከአለም የምግብ ፕሮግራም፣ 8 በመቶ ደግሞ ከሌሎች ዓለማቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ክልሎች  በበኩላቸው ከፌደራል መንግስት የሚደረገውን ድጋፍ በመረከብ ለተረጂዎች ያደርሳሉም ነው ያሉት።

‘ድጋፉ ለሁሉም ክልል በእኩል እየተደረገ አይደለም’ የሚሉ ቅሬታዎች አሉ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ምክትል ኮሚሽነሩ  ሲመልሱ ”መንግስት ምግብ፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ጨምሮ የእለት ደራሽ እርዳታውን በተረጂዎቹ ቁጥር ልክ ወደየአካባቢው በመላክ ላይ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል።

አልፎ አልፎ ከመረጃ ክፍተት፣ ከሚዲያ ሽፋን አለማግኘት፣ በመንገድ አለመመቻቸት፣ በጸጥታና በሌሎች ችግሮች ከሚገጥመው ክፍተት በስተቀር ክልሎች የተረጂዎችን ቁጥር ባሳወቁት መሰረት ድጋፉ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየተላከ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ መፈናቀል ቅጽበታዊ በመሆኑ የተረጂችን ቁጥር በአግባቡ አውቆ መረጃን ለሚመለከተው ለማድረስ አስቸጋሪ ከመሆኑ ባለፈ የክልሎችን የመረጃ አሰባሰብ አቅምንም የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ተረጂዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እራሳቸውን ማኖር እስከሚችሉበት ጊዜ ድረስ ድጋፉ ይቀጥላል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ።

ከሰብዓዊ ድጋፍ ጎን ለጎን በአካባቢ ውሃ ወለድ የሆኑትን  ጨምሮ  ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ከጤና ሚኒስቴር እና አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር ያሰማራቸው ከ200 በላይ የጤና ባለሙያዎች በየአካባቢው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑም ተመልክቷል። የመድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች የጤና መገልገያ ቁሳቁሶችም እየቀረበላቸው ነው ተብሏል። 

ተፈናቃቹን ወደቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ ሲሆን እስከ አሁን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።

ዜጎች ወደ ቀድሞ አብሮነታቸው እንዲመለሱና መፈናቀል እንዲቆም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።