በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ደዌ ሀረዋ ወረዳ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ሰላም ተመልሷል-ፖሊስ

112

ደሴ መጋቢት 27/2011 በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዌ ሀረዋ ወረዳ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደነበረበት ሰላም መመለሱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በስድስት ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ ታውቋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢኒስፔክትር መሐመድ ያሲን ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በደዌ ሀረዋ ወረዳ ቦራ ከተማ በሕብረተሰቡና በጸጥታ አካላት መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ወደ ነበረበት ሰላም ተመልሷል።

የግጭቱ ምክንያት መሳሪያ በመያዝ  እንስሳት የሚያግዱ ግለሰቦች ለከተማው የጸጥታ ደህንነት ስጋት በመሆናቸው የመሳሪያ አያያዛቸውን  እንዲያስተካክሉ የተነሳው ሀሳብ ህብረተሰቡ በመቃወም መሆኑን አመልክተዋል።

የጸጥታ ኃይሉ በሰላማዊ መንገድ ችግሩን ለማብረድ ቢሞክርም በተለያዩ አቅጣጫዎች የታጠቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በአሁን ወቅት የክልሉ ልዩ ኃይል ቦታው ላይ ደርሶ የማረጋጋት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሕብረተሰቡ፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በተደረገ ውይይት በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ወደ ነበረበት መመለሱን አስታውቀዋል፡፡

ከከሚሴ ወደ ደዌ ሀረዋ ወረዳ፣ ደሴ እና አዲስ አበባ የሚወስዱ መንገዶች በግጭቱ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ቢሆንም  ወዲያውኑ መከፈታቸውን ተናግረዋል።

ለጊዜው ተዘግተው የነበሩ የመንግስትና የግል ተቋማት ወደ ሥራ መግባታቸውን አመልክተው በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በየደረጃው ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለችግሩ መባባስ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ ከእውነት የራቀ መረጃ መሆኑን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተሩ ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ መረጃዎችን ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ማጣራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ከሀሰተኛ ወሬ ከመራቅ ባለፈ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት በመስራት የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቀም ጠይቀዋል።

አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲከሰትም ለጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የህግ የበላይነትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም