በመገንባት ላይ ያሉት የኢንዲስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደሥራ እንዲገቡ ጠንካራ ክትትል ይደረጋል ተባለ

63
አዲስ አበባ ግንቦት 25/2010 በኢትዮጵያ በመገንባት ላይ የሚገኙት የኢንዲስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው በፍጥነት ወደሥራ እንዲገቡ መንግስት የሚያከናውነውን ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ። ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ የአዳማና ድሬዳዋ ኢንዲስትሪ ፓርኮች በመጪው በጀት ዓመት ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል። በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል። የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ቦልኮ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ  በውጭ ብድር ከፍተኛ መዋለ ነዋይ የሚገነቡት የሀገሪቷን ምጣኔ ኃብታዊ መዋቅር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እንዲቻል ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸው ስለታመነበት ጭምር ነው። በመሆኑም ሀገራዊ ምጣኔ ኃብታዊ ፋይዳቸው ወሳኝ የሆኑት እነዚሁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው ጊዜ አንዲጠናቀቁ፤ በግንባታ ወቅትም ሆነ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ተግባር ሲገቡ የመልካም አስተዳደር፣ የአቅምና የአፈጻጸም ውስንነት እንዳይገጥማቸው ለማድረግ መንግስት ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል። ምክትል ሰብሳቢው አክለውም ኮርፖሬሽኑ በዘርፉ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል። ህብረተሰቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን በባለቤትነት እንዲመለከታቸው ማድረግ ይቻል ዘንድም ከክልሎችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚካሄደውን የቅንጅት ሥራ ማጎልበት እንደሚገባም አቶ መሀመድ አስገንዝበዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን በበኩላቸው ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን የአዳማና ድሬዳዋ የኢንዲስትሪ ፓርኮችን በመጪው በጀት ዓመት ወደ ሥራ ለማስገባት አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል። በፓርኮቹ የአንድ መስኮት አገልግሎትን ጨምሮ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ እና የቴሌ-ኮም አቅርቦቶችን  ለማሟላት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ሥራ አስፈፃሚው ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበርም በፓርኮቹ ሊሰማሩ የሚችሉ ባለኃብቶችን የመመልመል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። የአዳማና ድሬዳዋ ኢንዲስትሪ ፓርኮች ግንባታ የታሰበው ለባቡር ትራንስፖርትና እና ለወደብ አገልግሎት ያላቸውን ቅርበት በማጤን መሆኑን ጠቁመው በመጪው ዓመት ወደ ሥራ ሲገቡ የአገሪቷን የወጪ ንግድ ያሳድጋሉ ተብሎ እንደሚታመንም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው ተጠናቀው ወደ ሥራ ከገቡት የቦሌ ለሚ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌና ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጭ ያሉት ሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው 50 በመቶ ተጠኗቋል። በተለይ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክን በመጪው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አካባቢ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በሚነሱበት ወቅት ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ፣ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ፣ የመሰረተ ልማት እንዲሟላላቸውና በፓርኩ በሚፈጠሩ የስራ እድሎች ቀዳሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም  አቶ ሽፈራው አብራርተዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ አካባቢን እንዳይበክሉ ሀገሪቷ ከምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ መደረጉንም ጠቁመዋል። በሀገሪቷ ግንባታቸው የተጠናቀቁና እየተገነቡ ያሉትን ጨምሮ 11 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲኖሩ እነዚህም ቦሌ ለሚ አንድ፣ ቦሌ ለሚ ሁለት፣ መቀሌ፣ ሀዋሳ፣ ኮሞቦልቻ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ብርሃንና ሀረርቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም