የመስኖ አውታር ቀጣይነት ያለው ልማት ለማካሄድ እንደረዳቸው በሻሾጎ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ

88

ሆሳእና መጋቢት 26/2011 የመስኖ አውታር የዝናብ ወቅትን ሳይጠብቁ ቀጣይነት ያለው  ልማት ለማካሄድ እንደረዳቸው በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ

በዞኑ  ቦዮ ሐይቅን በመጠቀም በመስኖ የለማ መሬትና ያስገኘው ውጤት በመስክ ተጎብኝቷል፡፡

አርሶ አደር ደረበ ኤርጃቦ በሻሾጎ ወረዳ የጎልቾ ቦዮ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ዝናብን ብቻ ታሳቢ ያደረገ የግብርና ስራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በተወሰነ የዝናብ ወቅት ከሚከናውኑት የግብርና ልማት የማያገኙት ምርት ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር አመልክተው በአካባቢያቸው የሚገኘውን ቦዮ ሐይቅን በመጠቀም ከሌሎች ጋር ተደራጅተው አስር ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት የዝናብ ወቅትን ሳይጠብቁ በመስኖ በቆሎ ፣  ጥቅል ጎመን፣ የሀበሻ ጎመንና ሚጥሚጣ ቀጣይነት ባለው አካሄድ በማልማት ከፍጆታቸው አልፎ እየሸጡ ገቢያቸውን እንዳሳደጉ ነው፡፡

ቤተሰባቸውን በተገቢው ከማስተዳደር ባለፈ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት መገንባት ችለዋል።

የቀበሌው አርሶ አደር ደሳለኝ ቲርካሶ በበኩላቸው  ቦዮ ሐይቅ ላይ ከ2006ዓ.ም. አነስቶ መስኖ መጠቀም በመጀመራቸው ተጠቃሚ መሆናቸው ተናግረዋል።

በአንድ ለአምስት ተደራጅተው ከመንግስት በተመቻቸላቸው ጀነሬተር ስምንት ሄክታር መሬታቸውን  በማልማት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

በመስኖ ልማት ባገኙት ገቢ 80 ቅጠል ቆርቆሮ ቤት እንደሰሩና የውጭ ዝርያ ያላቸው አራት የወተት  ላሞች እንደገዙም አመልክተዋል፡፡

የመስኖ አውታር  በዝናብ ላይ ሳይወሰኑ ቀጣይነት ያለው  ልማት ለማካሄድ እንደረዳቸው አርሶ አደሮቹ በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ወቅት በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

የወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ደሳለኝ እንደገለጹት ከ14ሺ በላይ አርሶ አደሮችም ቦዮ ሐይቅን በመጠቀም  በመስኖ እያለሙ ናቸው፡፡

አርሶ አደሮቹ እያለሙ ያሉት ተደራጅተው እንደሆነና በየዓመቱ በአንድ ቀበሌ በሚገኙ ነዋሪዎች እስከ 600 ሺህ ብር እየቆጠቡ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የሀድያ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ እዮኤል ታደሰ በበኩላቸው  የመስክ ጉብኝቱ በየአካባቢው የሚገኘውን የውሃ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል  የሚያስችል ልምድ የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።

ቦዮ ሐይቅን ከቱሪስት መስህብ  ባሻገር አርሶ አደሩ ምርታማነቱን እንዲያሳድግበት  ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ ምቹ ሁኔታዎች እንደተፈጠሩ ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ52 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱንና ከዚህም ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም አመልክተዋል፡፡

በመስክ ጉብኝቱ ከዞንና ወረዳ የተወጣጡ አመራሮች ፣የግብርና  ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች  ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም