የባህርዳር ፈለገህይወት ሆስፒታል ኦክስጅን ማምረቻ ተመረቀ

120

ባህርዳር መጋቢት  26/2011 የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በባህርዳር ፈለገ ሕይህወት ሪፈራል ሆስፒታል ግቢ የተገነባውን የአማራ ክልል የህክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከልን መርቀው ከፈቱ።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይም የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንቷ በምረቃው ላይ እንደተናገሩት በባህርዳር የተገነባው የኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ከክልሉ አልፎ ለሀገሪቱም የሚያኮራ ተግባር ነው።

የማዕከሉ መገንባት የኦክስጅን አገልግሎት በወቅቱ ማግኘት ባለመቻላቸው ረጅም ዕድሜ መኖር እየቻሉ በአጭር የሚቀጩ ባርካታ ወላድ እናቶችና ህጻናትን ከሞት መታደግ የሚያስችል ነው።

“ማዕከሉ የመንግስትና የግል ባለሃብቱ ህብረት የታየበት በመሆኑ በምሳሌነት ሊወሰድ ይገባል”ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኦክስጅንን መሰረታዊ መድኃኒት ነው ብሎ በመመደቡ ኦክስጅን አቅርቦት በቀላሉ የሚገኝ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

“የክልሉ መንግስት መሰል የልማት ስራዎችን በማስፋፋት የክልሉን ህዝብ ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው” ያሉት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን ናቸው።

የማዕከሉ ስራ መጀመር ከዚህ ቀደም በክልሉ ህዝብ ጤና ላይ ይደርስ የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል።

“የአማራ ክልል መንግስት የክልሉን ህዝብ ህይወት በዘላቂነት የሚያሻሽሉ የክልሉን ዕምቅ የመልማት አቅም ወደ ተግባር በመቀየር የህዝቡን የኑሮ ደህንነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው”ብለዋል።

የፌዴራል ጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው  በክልሉ በባህርዳርና በደሴ ሆስፒታል የተገነቡ የኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከላት ስራ መጀመር የኦክስጅን ተደራሽነትን በማሳደግ በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት የህክምና ኦክስጅንን እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ መድሃኒቶች በማለት ከሚዘረዝራቸው ውስጥ እንደሚመደብ ገልጸው “ጽኑ ህሙማን ኦክስጅንን በግብዓትነት ይፈልጋሉ” ብለዋል።

“በኢትዮጵያ በብዙ የጤና ተቋማት ውስጥ አስተማማኝ የኦክስጅን አቅርቦት እጥረት እንዳለ ጥናቶች ያሳያሉ” ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ከ2016 ጀምሮ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በጤና ተቋማት ውስጥ የኦክስጅን አቅርቦትን ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ በርትቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

አሁን በሀገሪቱ ስድስት የደረሱትን የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከላት በቀጣይ ዓመት ወደ 13 በማሳደግ ሽፋኑን ከ20 ወደ 60 በመቶ ለማድረስ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

“የአማራ ክልል የህክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ስራ መጀመሩ ለኢትዮጵያዊያን መሰረታዊ የጤና ዘርፍ ዕድገት ማሳያ ነው” ያሉት ደግሞ የአሲስት ኢንተርናሽናል ፕሬዝደንት ራልፍ ሱድ ፊልድ ናቸው።

 “የአማራ ክልል የህክምና ኦክስጅን ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ የጤናው ዘርፍ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ የሚያበረክት ነው”ብለዋል።

በባህርዳርና በደሴ ተገንብተው ዛሬ የተመረቁት የኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከላት በቀን እያንዳንዳቸው ከ120 በላይ ኦክስጅን ሲሊንደር የማመረት አቅም እንዳላቸውም ታውቋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣በክልሉ መንግስት፣ በጀኔራል ኤሌክትሪክ ፋውንዴሽንና ግራንድ ቻሌንጅስ ካናዳ በተባሉ ድርጅት ትብብር የተገነቡት ሁለቱ ማዕከላት አጠቃላይ 80 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገባቸውም ለማወቅ ተችሏል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም