ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣለን-- -የኦዴፓ አባላትና ደጋፊዎች

63

ሀረር መጋቢት 26/2011 የሰላምና የልማት ሥራዎችን በማጠናከር ለውጡን ስኬታማ ለማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ በሐረሪ ክልልና በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሚገኙ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) አባላትና ደጋፊዎች ገለጹ።

ድርጅቱ የተመሰረተበት 29ኛ ዓመት በዓል ዛሬ በሐረር ከተማ ጨለንቆ ሰማዕታት የመሰብሰቢያ አዳራ ተከብሯል።

የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በወቅቱ እንደገለፁት ህዝብን ማዕከል ያደረገ የሰላምና የልማት ስራዎችን በማጠናከር ለለውጡ ስኬታማነት ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከድርጅቱ አባላት መካከል አቶ ነስረዲን አብዱረሃማን እንደተናገሩት "በዓሉ ክፍተቶችን ለይተን የተገኘውን ድል ይበልጥ ለማጠናከር ቃል  የገባንበት ነው" ብለዋል።

"የድርጅቱ አባላት ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጅምሮችን አጠናክረን በማስቀጠል ለለውጡ ስኬት እንተጋለን" ብለዋል ።

"የሰላምና የልማት ስራዎችን በማጠናከር ለውጡን ስኬታማ ማድረግ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ኃላፊነት ነው" ያሉት  ደግሞ ወይዘሮ አሊያ ሁሴን ናቸው ።

ከሌሎች እህትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለተግባራዊነቱ በትጋት እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

ወጣት ኤሊያስ አብዱሰቡር በበኩሉ " ወጣቶች የሰላምና የልማት ስኬታማ ተሞክሮዎችን በማጠናከር ለውጡን ወደ ፊት ለማራመድ እንሰራለን " ብሏል።

የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ "በዓሉ የውይይትና የመደማመጥ ባህልን በማጎልበት ለቀጣይ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎችን ለማጠናከር በጋራ ቃል የገባንበት ነው" ብለዋል ።

በፖለቲካው የተገኘውን ድል በኢኮኖሚው ዘርፍ በመድገም ሀገራዊ ለውጡን ማሳካት እንደሚገባም አመልክተዋል።

"የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን የተመዘገቡ ድሎችን በመጠበቅ ለውጡን ማስቀጠል ይጠበቅብናል" ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል ።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው "የሐረሪ ብሔራዊ ሊግና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ  ህዝቡ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ስራዎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን በጋራ እየሰራን ነው" ብለዋል ።

"የሊጉ አባላትና ደጋፊዎች ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ጎን በመሰለፍ በህዝብ መስዋትነት የተመዘገበውን የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ  አጠናክረን ለማስቀጠል እንሰራለን" ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

የአዴፓ፣ ህውሓትና ደኢህዴን ተወካይዎችም ኦዴፓ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን አጠናክሮ ለማስቀጠል የያዘውን ግብ ለማሳካት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም