ኢንስቲትዩቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

103
አዳማ ግንቦት 25/2010 የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍን በምርምርና ጥናት በመደገፍ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ። ኢንስቲትዩት ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር ከክልሉ ለተወጣጡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አካላት  ያዘጋጀው የአቅም  ግንባታ ስልጠና በአዳማ ከተማ ተካሄዷል፡፡ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ስነስርዓት ወቅት በኢንስቲትዩቱ የፈጻሚዎች ልማትና ስልጠና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጥሩወርቅ ገብረማሪያም እንዳሉት መስሪያ ቤታቸው በሁሉም የኮንስትራክሽን ዘርፎች ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ ነው። በተለይ ዘርፉን በጥናትና ምርምር ከሚገኙ ውጤቶች በመደገፍ ወደ ኢንደስትሪው ለማስፋፋትና ለማስረጽም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚገኙ አመራሮች፣ ፈጻሚዎችና ባለሙያዎችን አቅም ለመገንባትም ካለፈው ዓመት ወዲህ ልዩ ትኩረት ሰጥቶት በመስራት ላይ እንደሚገኝና የአዳማው ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን አስታውቀዋል። ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር በመተባበር በክልሉ ለሚገኙ የዘርፉ አካላት የተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና ያተኮረው በኮንስትራክሽን ስነ ምግባር፣በፕሮጀክትና በዋጋ ዝርዝር እቅድ እንዲሁም የፕሮጀክት ስጋት አስተዳደርና ግዥ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። "ይህም በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ዙሪያ ያለውን የአፈጻጸም ችግር ከመፍታት ባሻገር ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ  ይረዳል" ብለዋል ዳይሬክተሯ። የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጎሳ ፈይሳ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ የፕሮጀክቶች መጓተት ችግር ሲያጋጥም መቆየቱን ተናግረዋል። ህብረተሰቡም ከልማት ፕሮጀክቶቹ ተጠቃሚ መሆን ባለመቻሉ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱንም አስረድተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠቱ በክልል፣ በዞንና በከተሞች የዘርፉን መዋቅር በመዘርጋት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በቢሮው የመንግስት ግንባታ ፕሮጀክቶች ዲዛይን አጽዳቂና የክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ በዳሳ ጅንፌሳ በሰጡት አስተያየት "ስልጠናው በፕሮጀክት ማኔጅመንት ዙሪያ ያለውን ሰፊ የእውቀት ክፍተት ይሞላል" ብለዋል። በተለይ የክትትልና ቁጥጥር ስልቱን በማጠናከር በመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚታየው የግንባታ መዘግየት ችግር  እንደሚያቃልልም አመልክተዋል። ኢንስቲትዩት ለአምስት ቀናት ያዘጋጀውና ትናንት በተጠናቀቀው የአቅም ግንባታ ስልጠና  ከኦሮሚያ ክልል የተወጣጡ  የኮንስትራክሽን ዘርፍ አመራሮች፣ ፈጻሚዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም