እንቦጭን በዘመቻ ለማስወገድ እየሰሩ መሆናቸውን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

85

አርባምንጭ መጋቢት 26/2011 በአባያ ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከነዋሪዎች መካከል አቶ ታከለ አንበሴ ለኢዜአ እንዳሉት የአባያ ሐይቅ በቱሪስት መስህብነቱ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡

በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በሐይቁ ላይ ተመስርተው ሕይወታቸውን እየመሩ መሆናቸውን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ሐይቁ በእንቦጭ አረም መወረሩ ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

በእዚህም ካለፈው ወር ጀምሮ አረሙን ለማስወገድ እየተደረገ ባለው ዘመቻ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይም አረሙ እስኪወገድ ድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

ሌላኛው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ አቶ አይኖሼ ሸንካ በበኩላቸው በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በወቅቱ ማስወገድ ባለመቻሉ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

" ከጣና ሐይቅ በመማር በዓባያ ሐይቅ ዳር ያንዣበበውን የእንቦጭ አረም ከአቅም በላይ ከመሆኑ በፊት ተረባርቦ ማስወገድ አማራጭ የለውም " ብለዋል፡፡

መንግስትና ሕብረተሰቡ አረሙን ለማስወገድ የጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው እርሳቸውም ተስፋ ሳይቆርጡ የጀመሩትን አረሙን የማስወገድ ሥራ ለማጠናከርና ሌሎችንም ለማነሳሳት ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የእንቦጭ አረሙ የተከሰተበትን ስፍራ በተጨባጭ ባለመገንዘብ እንደ አዞና ጉማሬ ያሉ የውሃ ውስጥ እንስሳት ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ገብቷቸው እንደነበር የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ፀሐይ ተሸሜ ናቸው፡፡

"አረሙ የተከሰተው ከሐይቁ ዳር በእጅ ነቀላ ማስወገድ በሚቻልበት ስፍራ በመሆኑ ስጋቴን ቀንሶታል" ብለዋል።

አረሙን በማስወገድ ተግባር የአካባቢው ሕብረተሰብ ተሳትፎ እያደረገ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ ሕብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ጥሪ አቅርበዋል።

የጋሞ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማዜ ሸቀነ በበኩላቸው "ከ2ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው የአባያ ሐይቅ ክፍል በእንቦጭ አረም ተወሯል" ብለዋል፡፡

ለአንድ ወር አረሙን በዘመቻ ለማስወገድ በተደረገ እንቅስቃሴ 100 ሄክታር የሚጠጋ የአረሙ ክፍል ላይ የነበረ አረም መወገዱን ጠቁመው በቀጣይም አረሙ ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ ጥረቱ ሳይቋረጥ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የእንቦጭ አረሙ በእጅ ተነቅሎ መወገድ የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም