የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የአርሜኒያ መንግስት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

1143

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2011 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የአርሜኒያ መንግስት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ  ከአርሜኒያ ጋር በጋራ እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም ሁለቱ አገሮች ያላቸውን የረዥም አመታት ወዳጅነት በመጠቀም በመንግስትና መንግስት መካከል እንዲሁም በመንግስትና በቢዝነስ ሴክተሩ መካከል የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን የማበልጸግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ አገሮች እስካሁን ባላቸው የትብብር ስራዎች የአርሜኒያ መንግስት በኢትዮጵያ ባሉ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚተከሉና የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግና የሒሳብ ትምህርትን የሚደግፉ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ቁሳቁሶቹ በቁጥር 50 ሲሆኑ እያንዳንዳቸው 30 ሺህ ዶላር የሚያወጡ የላቦራቶሪ ዕቃዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህም የፈጠራና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርትን የሚደግፉ መሳሪያዎች በተለይ ወጣቶች በፈጠራ ስራ ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአርሜኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዞህራብ መናተሳ ካናያን በበኩላቸው እንዳሉት፤ የፈጠራና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራ ለሰው ልጆች የእለት ተለት እንቅስቃሴ እጅግ ወሳኝ ናቸው።

በዚህም አርሜኒያ በኢኖቬሽን ፣ በፈጠራና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ  አርሜኒያ ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈልና በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ወዳጅነት የነበራት አርሜኒያ ተቀዛቅዞ የቆየውን ግንኙነቷን ለማጠናከር በቅርቡ ኤምባሲዋን ትከፍታለች።