ያልዘሩትን ማጨድ….

198


ዜናው ፈንቴ( ኤዜአ)

ጥሩ መሪዎች የጥሩ ተመሪዎች ውጤት ናቸው፡፡ ጥሩ መሪ እንዲኖር ጥሩ ተመሪ ሊኖር ግድ ይላል፡፡ ጥሩ ተከታይ በሌለበት ጥሩ መሪ ማውጣት አይቻልምና፡፡ ጠንካራ ተከታዮች ካሉ የመሪያቸው ጠንካራ ጎኖች ይበልጥ እንዲጎለብት ፤ ደካማ  ጎኖቹ ደግሞ እንዲሻሻል በማድረግ  የመሪ ምሰሶ ይሆናሉ። ጠንካራ ተከታዮች መሪያቸው ብቃት ከጎደለው በጊዜ በሌላ የተሻለ መሪ እንዲተካ ማድረግ እንደሚችሉ ሁሉ ደካማ ተከታዮች ግን ጠንካራውን መሪ ያዳክማሉ፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የአመራር ድክመት መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ተከታዮችን/ተመሪዎችን መመዘን አንዱ መንገድ  ነው። ተከታዮችም የአመራር ችግር ገጠመን እያሉ ከማማረራቸው በፊት እኛ እንዴት ያለን ተከታዮች ነን? ብለው ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል።  

ስኬታማ አመራር ለማስፈን፤ ለአላማቸው መሳካት ዋጋ ለመክፈል የቆረጡ፣ የጋራ ውጤት የሚገኘው በጋራ ጥረት መሆኑን የተረዱ፣ መብትና ግዴታቸውን የተገነዘቡ፣ በራሳቸው የሚተማመኑና ለሚሰሩት ስራ ሃላፊነት የሚወስዱ ተመሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህን ባህሪያት ሳይላበሱ ጥሩ መሪም ሆነ ጥሩ አመራርን መፈለግ ማሽላ ዘርቶ ስንዴ  እንደመጠበቅ ይቆጠራልና፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የመሪ ዋና ሚና ራዕይ ማጋራትና የህዝብ ፍላጎትን በተደራጀ መልኩ መምራት እንዲሁም ዜጎች ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ ለሚያደርጉት ጥረት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡ ቀጣይነት ያለው ልማትንም ሆነ አስተማማኝ ዴሞክራሲን ማረጋገጥ የሚቻለው መንግስት የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ያወጣቸውን አሰራሮችንና መመሪያዎችን ተከትሎ ህዝብ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ  ብቻ ነው፡፡

ስኬትም ሆነ ውድቀት የመንግስት/የመሪ/ እና የህዝብ ስራ ድምር ውጤት ነው፡፡  መንግስት ብቻውን ልማትንም ሆነ ዴሞክራሲን ማረጋገጥ ስለማይችል፤ሁለቱም ወገን በስኬት ጊዜ ምስጉን በውድቀት ጊዜ ደግሞ ተወቃሽ ናቸው፡፡

ህዝብም ቢሆን ባልተጠና ፖሊሲና ባልተደራጀ አመራር ልማትንም ሆነ ዴሞክራሲን ማምጣት አይቻልም፡፡ መንግስትና ህዝብ ተናበውና ጎዶሎዎቻቸውን እየተራረሙ ከሄዱ ግን ስኬትን ማረጋገጥ የማይቻልበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፡፡

ለውጥ ሰዎች አሁን ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ ወደ ተሻለ ሁኔታ የሚሸጋገሩበት ሂደት ነው፡፡ ይህ ሲባል መሪም ሆነ ሌሎች ሰዎች ውስብስብና ፈታኝ የሆነውን የውድድር አለም በአሸናፊነት ለመወጣት አዳዲሰ ስትራቴጅዎችንና ስልቶችን የሚቀይሱበትና አሰራራቸውን የሚያሻሽሉበት ሂደት ነው፡፡  በኢትዮጵያም አሁን  ያለነው ለውጥ ላይ ነው፡፡

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አሁን በአገራችን የመጣውን ለውጥ ካወቅንበት ለቀጣይ መፃይ እድላችን መሰረት የምናስቀምጥበት ወይም ደግሞ በተቃራኒው ወደማንወጣው የእርስ በእርስ ትርምስ የምንገባበት ምዕራፍ ላይ ነን፡፡ ከነዚህ ሁለት የከፍታና የቁልቁለት አማራጮች አንዱን መያዝ የኛ ምርጫ ነው፡፡

የመጀመሪያው የመጣውን ለውጥ በመደገፍና የጋራ ጠላታችን የሆነውን ኋላ ቀርነትና ድህነትን በተባበረ ክንድ አሽቀንጥረን በመጣል አንድነታችንንና ብልዕግናችንን ማረጋገጥ እንዲሁም  የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ውህደት አርአያነታችንን አስጠብቆ መቀጠል ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ከኋላቀርነትና ድህነነት ጋር ተስማምቶ  መኖር ነው፡፡ ሁለተኛውን አማራጭ የሚመርጥ ሰው አለ ብዬ ባላምንም ምን ያህል መንታ መንገድ ላይ እንዳለን ግን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ለውጥ መፈለጋችን፣ የተሻለ ህይወት መኖር መሻታችን ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በለውጡ ማግስት በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎች ምስክሮች ናቸው፡፡ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ያ የሞቀው ድጋፍ፣ የመለወጥ ፊላጎት ማሳያ የነበሩት አንዳንድ አካላትና ድርጀቶች በሚያቀነቅኑት ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ሲገባቸው ጥርጣሬ ለመፍጠር እየሰሩ በመሆኑ ጥቂት የማይባል የህብረተሰብ ክፍል መደነጋገሩ አልቀረም፡፡

ይህ ነው እንግዲህ ለውጡን መንታ መንገድ ላይ ነው ያስባለው፡፡ ለውጡን ለማደናቀፍ ወደ ግላዊ  ብልፅግና ማማ ለመውጣት በስሜት ፈረስ የሚጋልቡ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች አደብ መግዛት ይኖርባቸዋል። የያዙት አቋም ያለንበትን ክፍለ ዘመን የማይመጥን መሆኑን መገንዘብ

ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሃይሎች ግራና ቀኝ መሳሳቡን ትተው በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን በማምጣት ለለውጥ ሂደቱ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ህዝቡም  ከእኩይ አላማ ማስፈፀሚያ መሳሪያነት ወጥቶ ሽ-ዘመናትን አብሮ ከዘለቀው ወገኑ ጋር የሚጠበቅበትን በጎ ተግባር በመፈጸምና አንዱ ለአንዱ አለኝታነቱን በማሳየት ጥሩ ተመሪ ከሆነ ህልማችን ይሳካል። ይህ ካልሆነ ግን ለውጥ ከራስ ካልጀመረ ከየትም አይመጣምና ሁሉም በትኩረት ልያጤነው ይገባል።  ሰላም!   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም