በአምቦ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ የማዕድን ቦታዎች፣ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች ለሥራ አጥ ወጣቶች ተላለፉ

64

አምቦ መጋቢት25/2011 በአምቦ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ የማዕድን ቦታዎች፣ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችን ለሥራ አጥ ወጣቶች መተላለፋቸውን የከተማዋ ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጀግናው ግዛው እንዳስታወቁት በከተማዋ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙትን 67 የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችና 36 ሄክታር የማዕድን ማምረቻዎች የተላለፉት ባለፉት ሰባት ወራት ጥናት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ በማድረግ ነው።

ከነዚህም በማይገባቸው ግለሰቦች እጅ የነበሩ ሼዶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው በ62 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 202 ወጣቶች ተላልፈዋል፡፡

ወጣቶቹ በሼዶቹ በመጠቀም በማምረቻ፣ በንግድና በሌሎች የገቢ ማስገኛ መስኮች መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡

እርምጃው ተደራጅተው የመስሪያ ቦታ በማጣት የሚንገላቱ ወጣቶችን ችግር ማቃለሉን ኃላፊው አስረድተዋል።

ሼዶችን የተረከቡት ኢንተርፕራይዞች ለአምስት ዓመታት ከተገለገሉ በኋላ ለሌሎች አንቀሳቃሾች  ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ከተፈቀደው ዓላማ ውጪ በባለሀብቶች መጠቀሚያ የነበረ 36 ሄክታር የማዕድን ማምረቻዎችን በተመሳሳይ ሁኔታ ተነጥቀው ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች መሰጠቱን ነው ያመለከቱት።

ከእድሉ ተጠቃሚዎች መካከል ወጣት ባዩሽ ንጉሴ በሰጠችው አስተያየት በከተማው የተገነቡት ሼዶች በማይገባቸው ግለሰቦች ተይዘው የነበሩ ሼዶች ስለተሰጣቸው ችግራቸው መቃለሉን ተናግራለች።

ወጣት መርጊቱ ጫላ በበኩሏ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ሥራ ለመሰማራት የቦታ ጥያቄ ካቀረቡ ሰባት ወራት እንዳስቆጠረ አስታውሳ፣ አሁን በመሥሪያ ቦታ እጦት የነበረባቸው ችግር መቃለሉን ገልጻለች።

በአምቦ ከተማ በዚህ ዓመት ተደራጅተው ወደ ሥራ ውስጥ ለገቡ 4 ሺህ ወጣቶች አንድ ሚሊዮን ብር ብድርን ጨምሮ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ተሰጥቷቸዋል።

ወጣቶቹ በእንቅስቃሴያቸው ውጤታማ እንዲሆኑም ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም