አርሜኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ልትከፍት ነው

64

አዲስ አበባ  መጋቢት 25/2011 አርሜኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ዳግም ለማጠናከር ኤምባሲዋን በቅርቡ በአዲስ አበባ እንደምትከፍት ገለጸች።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአርሜኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዞህራብ መናተሳ ካናያን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ዳግም እንዲጠናከር ትፈልጋለች።

በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት፤ ሁለቱ አገሮች ዘመናትን ያስቆጠረ ትስስራቸውን በማደስ የተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ ለጋራ ተጠቃሚነት ይሰራሉ።

ኢትዮጵያና አርሜንያ ግንኙነታቸው ጠንካራ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አሸብር ባለፉት አመታት ግን ተቀዛቅዞ መቆየቱን ጠቁመዋል።

ወዳጅነቱን መልሶ ለማደስና ለማጠናከር አርሜኒያ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ የመክፈት ፍላጎት እንዳላት የአርሜኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጻቸውን አቶ አሸብር ተናግረዋል።

አርሜኒያውያን ከ50 አመታት በፊት በኢትዮጵያ እንደ ዜጋ የሚቆጠሩበት ሁኔታ እንደ ነበር በመግለጽ፣ በሚጠናከረው ግንኙነት በመታገዝ የአገሪቱ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክ ንግድ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የአገሮቹ ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።

በተለያዩ ዘርፎች ላይ በሚደረጉ ውይይቶችና ትብብሮች ላይም ሁለቱ አገራት በጋራ በመሳተፍ ጠንካራ ግንኙነት ለመመስረት እንደሚሰሩ መወያየታቸውን አቶ አሸብር አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም