ድርጅቱ በሰመራ በ20 ሚሊዮን ብር ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው

56

ሰመራ መጋቢት 25/2011 በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ ደረጃውን የጠበቀ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ትምህርት ቤት  የመሠረተ ድንጋዩን ትናንት ያስቀመጡት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ናቸው።

በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ግንባታው ለሚጠናቀቀው ትምህርት ቤት 800 ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

ትምህርት ቤቱ 16 የመማሪያ ክፍሎች፣ቤተ መጻህፍት፣ቤተ ሙከራና የአስተዳደር ክፍሎች ይኖሩታል።

እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያዎችና አረንጓዴ ሥፍራዎች እንደሚኖሩት ተመልክቷል።

አቶ አወል የመሠረተ ድንጋዩን ባስቀመጡበት ወቅት ድርጅቱ ትምህርት ቤቱን ለመገንባት ያሳየው ተነሳሽነት ለሌሎች ባለሃብቶች በአርአያነት ይታያል።

የክልሉ መንግሥት ከኢንቨስትመንት ሁሉ የላቀ ኢንቨስትመንት የላቀው የሰው ኃይል ኢንቨስትመንት መሆኑን በማመን ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል።

የድርጅቱ ባለቤት አቶ ሲሳይ ደስታ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት ድርጅቱ ትምህርት ቤቱን የሚገነባው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትና የክልል መንግሥትና ሕዝብ ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋና ለማቅረብ ጭምር እንደሆነም ተናግረዋል።

ልማት በመንግሥት ውስን በጀት ብቻ ስለማይከናወን የግል ባለሃብቶችና ሕዝቡ ድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።

በዝግጅቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም