የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ያልተቆጠበ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ ቀረበ

አሶሳ መጋቢት 24/2011 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ህዝቡ ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

የግድቡ ግንባታ ሥራ የተጀመረበት 8ኛ ዓመት በዓል ግንባታው በሚካሄድበት ጉባ ወረዳ ዛሬ ተከብሯል፡፡

የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን በወቅቱ እንደገለጹት የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያንን የይቻላል መንፈስ ለዓለም ህዝብ በገሃድ ያሳየ ነው፡፡

"በአብሮነት ከቆምን ተግባራዊ ለውጥ ማምጣት እንደምንችል የግድቡ ግንባታ በተግባር አረጋግጧል" ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ የአገራችንን ታላቅነት ከሚያውጁ ፕሮጀክቶች አንዱ እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ስምንት ዓመታት ሥራው በሚፈለገው ልክ መከናወን እንዳልቻለ ተናግረዋል።

" ግንባታውን አጠናቀን ለትላልቅ  ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ምሳሌ ልናደርገው ይገባል " ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ሥራ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ህዝቡ በአንድነት መንፈስ ሲያደርግ የቆየውን ያልተቆጠበ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ሂደት ሁሉ መንግስት ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግበት ሁኔታ አመቻችቷል።

የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው በግድቡ ግንባታ የባከነውን ጊዜ በማካካስ ለፍጻሜ እንዲበቃ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በግድቡ ግንባታ መዘግየት ቅር የተሰኘውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለመካስ ጠንክረን እንሠራለን" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብረሃም በላይ በበኩላቸው የግደቡ ህልውና እውን የሚሆነው ሥራው ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

" በአሁኑ ወቅት የግድቡ አጠቃይ የግንባታ ሥራ 66 በመቶ ተጠናቋል " ብለዋል።

በበዓሉ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል  ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም