የኢትዮጵያን ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ወጣቶች የመሪነት ሚና መጫወት አለባቸው_ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይ

58
አዲሰ አበባ ግንቦት 24/2010 የኢትዮጵያን ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ወጣቶች የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይ አህመድ አስገነዘቡ። ወጣቶች በበኩላቸው በየደረጃው የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ከቶኒ ብሌየር ለዓለም ለውጥ ተቋም ጋር በመቀናጀት "የነገዋ ኢትዮጵያ መሪዎችን ማነቃቃት" በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ ወጣቶች የአነቃቂ ንግግር ዝግጅት አካሄዷል። በዝግጅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር እና የ'ማይክሮ ሶፍት ፎር አፍሪካ' ቀጣናዊ ዳይሬክተር አምሮቴ አብደላ ወጣቶች ነገን የመረከብ ሃላፊነታቸውን በሚወጡበት ርዕስ ላይ ያተኮረ ንግግር አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት፤ የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ በወጣቶች ተሳትፎ ይመጣል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'ወጣቶች በውሳኔ ሰጭነትና አመራርነት ቁልፍ ሚና መጫወት አለባቸው' ሲሉ መልዕክት አስተላለፈዋል። መንግስት ወጣቶች በአገራቸው ሁለንተናዊ ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የአገሪቷን አቅም ባገናዘበ መልኩ ምቹ እድሎችን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር ወጣቶች በርካታ ነገሮችን ለመመርመር እዕምሯቸውን ክፍት እንዲያደርጉ መክረው፤ በተለይ ልዩነቶችን እንደ ስጋት ሳይሆን እንደመልካም አጋጣሚ እንዲወስዷቸው ጠይቀዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው በዝግጅቱ የተገኙ ወጣቶች በበኩላቸው በየጊዜው የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው በየተሰማሩበት ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ወጣት አቤል አንዳለ 'የሚገጥሙን ችግሮች ሊያጠነክሩን እንጂ ሊያስፈሩን አይገባም' ብሏል። ችግሮች ቢገጥሙንም አባቶቻችን ብዙ ለፍተው ያስረከቡንን አገር የተሻለች የማድረግ ሃላፊነት አለብን ስትል የተናገረችው ደግሞ ወጣት ዘጸዓት አበበ ናት። የቶኒ ብሌየር ለዓለም ለውጥ ተቋም በቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር የሚመራና በሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ብዙሃኑን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻልን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም