በኬንያ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያኖች ይፈታሉ ተባለ

98
ናይሮቢ 29/2010 ኬንያ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያኖችን ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን አስታወቃለች፡፡ ኢትዮጵያና ኬንያ ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከርም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። በውይይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በኬንያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያኖች እንዲፈቱ የኬንያውን ፕሬዚዳንት ጠይቀው ፤ ከፕሬዚዳንቱም ይሁንታን አግኝተዋል። ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ናይሮቢ በገቡበት ወቅት ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ጋር ተወያተዋል። በሁለትዮሽና በቀጠናዊ ጉዳይ ላይ ምክክር ያደረጉት ሁለቱ መሪዎች ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ተስማምተዋል። ሞያሌን የምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ኃብት እምብርት ለማድረግም በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ላይ ደርሰዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኬንያ አየር መንገድ በትብብር እንዲሰሩ፤ እንዲሁም የላሙ ወደብን በጋራ ለማልማት መስማማታቸው ተገልጿል። ከዛም ባለፈ በቱሪዝም ዘርፍ በቅንጅት ለመሥራት መሥማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለሰ ዓለም አስታውቀዋል። የምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ኃብት የኃይል ቋት የሆኑት ኢትዮጵያና ኬንያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም