ጣሊያን የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎች ድጋፍ አደረገች

104

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2011 የጣሊያን መንግስት በምግብ ውስጥ የሚገኘውን ገንቢ የንጥረ ነገር መጠን መለካት የሚያስችሉ ሁለት የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎች ድጋፍ አደረገ።

በጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ በኩል የተላለፉት መሣሪያዎች  80 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወጪ ተደርጎባቸዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መሳሪያዎቹን ተረክቧል።

በኢንስቲትዩቱ የምግብ ሳይንስና ኒውትሪሽን ላቦራቶሪ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ መሰረት ወልደዮሃንስ እንደገለጹት፤ መሣሪያዎቹ በምግብ ውስጥ ያለውን የስብና የአሚኖ አሲድ ንጥረ ነገር መጠን ለመለካት ስለሚያስችሉ የሕክምና ሥራውን ያግዛሉ።

ኢንስቲትዩቱ እንዲህ ያሉ መሣሪያዎች ያልነበሩት በመሆኑ የምርምር ውጤቱን ውስብስብ አድርጎበት እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን የተረከቡት የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎች የምርምር ሥራውን ቀልጣፋና ተአማኒ እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በተለይም በሰው ውስጥ ያለውን የአሚኖ አሲድ መጠን ከደም በተወሰደ ናሙና ለማወቅ የሚያስችል መሆኑንም አቶ መሰረት አክለዋል።

መሳሪያዎቹ በምግብ ውስጥ ያለውን የስብ መጠን እንደሚለኩ ያብራሩት አስተባባሪው ''ይህም እያንዳንዱ የምግብ አይነት ያለውን የቅባት መጠን ለማወቅ ያግዛል'' ብለዋል።

ይህ መሳሪያ ከእንስሳት ተዋጽኦና ከቅባት እህሎች ባሻገር ለምግብነት የሚውለውን የሞሪንጋ ቅጠል የስብ መጠንን የሚለካ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሞሪንጋ የስብ መጠኑ ከቅባታማ እህሎችና ከእንስሳት ተዋጽኦ እኩል እንደሆነ በመጠቆም ይህም መጠኑን በምርምር እንዲደገፍና አጠቃቀሙ ላይ ጥናት ለማካሄድ ያግዛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ኃላፊ ቲቤሪዮ ቺያሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጣሊያን ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ኤጀንሲው የድርሻውን ይወጣል።

በተለይም በጤናው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ ድጋፎችን በቀጣይ እንደሚያደርጉ በመጠቆም ከሌሎች የምርምር ተቋማትና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር እንደሚሰራ አክለዋል።

በተለይም ሴቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፎአቸውን እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም