በቅሎ ወለደች

653

 ደብረ ብርሃን  መጋቢት 24/2011 ለወትሮ በቅሎ የሚወለደው አህያ ከፈረስ ጋር ስትዳቀል ነው ይባል ነበር፤ ሰሞኑን ከሰሜን ሸዋ ጣርማ በር ወረዳ የተሰማው ዜና ግን ከእዚህ የተለየና ያልተለመደ ነው።

አንዲት በቅሎ ባለተለመደ ሁኔታ አምሳያዋን መውለዷ ተሰምቷል።

ምናልባት እርስዎ በትምህርትና በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያውቁት በቅሎ በዘር መውለድ እንደማትችል ይሆናል፤ ከእዚህ የተነሳ የእዚችን በቅሎ መውለድ ሲሰሙ በአዕምሮዎ እንዴት? የሚል ጥያቄ ያጭርብዎት ይሆናል።    

በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ ሰሞኑን የተከሰተው እውነታ ግን ብዙዎችን የአካባቢው ነዋሪዎች ከማስግረም አልፎ አስደምሟል።

የጣርማ በር ወረዳ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው በመዘዞ ንኡስ ወረዳ ኮሶበር ቀበሌ መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ለሊት ላይ አንዲት በቅሎ አምሳያዋን ግልገል በመውለድ ብዙዎችን አስደንቃለች።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በቅሎዋ የወለደችው ባልተለመደ ሁኔታ ነው።

በአካባቢው በርከት ያለ በቅሎ ቢኖርም ከእዚህ ቀደም እንዲዚህ አይነት ክስተት ተከስቶ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡

የበቅሎ ባለቤት አቶ ሙላት ኃይለሚካኤል በበኩላቸው በቅሎዋን በ2009 ዓ.ም ገዝተው ሲገለገሉባት መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

" የበቅሎዋ ሰውነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወፈረ መምጣቱንና ጡቶቿ ማጋቷን ብመለከትም እርግዝና ይሆናል ብዬ አልገመትኩም" ብለዋል።

በበቅሎዋ መውለድ መገረማቸውን የገለጹት አቶ ሙላት፣ የተወለደችው ሴት ግልገል በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

እናትያዋም የወለደቻትን ግልገል በማጥባት ላይ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በጣርማ በር ወረዳ እንስሳት ሃብት ጽህፈት ቤት የእንስሳት ጤና ባለሙያ አቶ ዘላላም ደምሴ በበኩላቸው አህያ ከፈረስ ጋር ተዳቅላ በቅሎ ስትወልድ ማየት የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

"በኮሶበር ቀበሌ ሰሞኑን የሆነው ክስተት ግን ከእዚህ እውነታ የተለየና ያልተመደ ነው" ብለዋል።

በቅሎ በዘር እራሷን መተካት እንደማትችል ቢታወቅም እንዲህ አይነት ክስተት ከአንድ ሚሊዮን በቅሎዎች መካከል በአንዷ ላይ ሊከሰት  እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም